1 ዜና መዋዕል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለካህናት የተሰጠ የሥራ ኀላፊነት 1 የአሮን ልጆች የሚከተሉት ናቸው፦ አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ተብለው የሚጠሩ ናቸው፤ 2 ናዳብና አቢሁ ምንም ዘር ሳይተኩ አባታቸው ከመሞቱ በፊት ሞቱ፤ ስለዚህ የእነርሱ ወንድሞች አልዓዛርና ኢታማር ካህናት ሆኑ፤ 3 ንጉሥ ዳዊት የአሮንን ዘሮች እንደየሥራ ምድባቸው በቡድን በቡድን ከፈላቸው፤ ይህንንም ያደረገው የአልዓዛር ዘር በሆነው በሳዶቅና የኢታማር ዘር በሆነው በአቤሜሌክ ረዳትነት ነው። 4 የአልዓዛር ቤተሰብ ቊጥር ከኢታማር ቤተሰብ ቊጥር በልጦ ስለ ተገኘ አመዳደቡም በዚሁ መሠረት ተወሰነ፤ ስለዚህ የአልዓዛር የቤተሰብ አለቆች ቊጥር ዐሥራ ስድስት ሆኖ ሲደለደል የኢታማር አለቆች ቊጥር ስምንት እንዲሆን ወሰነ። 5 በአልዓዛርና በኢታማር ዘሮች መካከል የቤተ መቅደስ ባለሥልጣኖችና መንፈሳውያን መሪዎች ይገኙ ስለ ነበር፥ የሥራ መደብ ክፍፍል የሚደረገው በዕጣ ነበር። 6 ዕጣውንም በቅድሚያ ለማውጣት የአልዓዛርና የኢታማር ዘሮች ተራ ይገቡ ነበር፤ ከዚህም በኋላ በሌዋዊው ጸሐፊ በናትናኤል ልጅ በሸማዕያ ይመዘግቡ ነበር፤ ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች፥ ካህናቱ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ፥ እንዲሁም የካህናትና የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ሁሉ ምስክሮች ነበሩ። 7-18 ኻያ አራቱ የቤተሰብ ቡድኖች በዕጣ የወጣላቸው የሥራ ምድቡ ክፍፍል ቅደም ተከተል ተራ እንደሚከተለው ነው፦ አንደኛ በይሆያሪብ የሚመራው ቡድን፥ ሁለተኛ በይዳዕያ የሚመራው ቡድን፥ ሦስተኛ በሐሪም የሚመራው ቡድን፥ አራተኛ በሰዖሪም የሚመራው ቡድን፥ አምስተኛ በማልኪያ የሚመራው ቡድን፥ ስድስተኛ በሚያሚን የሚመራው ቡድን፥ ሰባተኛ በሀቆጽ የሚመራው ቡድን፥ ስምንተኛ በአቢያ የሚመራው ቡድን፥ ዘጠነኛ በኢያሱ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥረኛ በሸካንያ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ አንደኛ በኤልያሺብ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ሁለተኛ በያቂም የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ሦስተኛ በሑፓ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ አራተኛ በዬሼብአብ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ አምስተኛ በቢልጋ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ስድስተኛ በኢሜር የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ሰባተኛ በሔዚር የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ስምንተኛ በሃፒጼጽ የሚመራው ቡድን፥ ዐሥራ ዘጠነኛ በፐታሕያ የሚመራው ቡድን፥ ኻያኛ በይሔዝቄል የሚመራው ቡድን፥ ኻያ አንደኛ በያኪን የሚመራው ቡድን፥ ኻያ ሁለተኛ በጋሙል የሚመራው ቡድን፥ ኻያ ሦስተኛ በደላያ የሚመራው ቡድን፥ ኻያ አራተኛ በማዓዝያ የሚመራው ቡድን። 19 እነዚህም ሰዎች የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የቀድሞ አባታቸውን አሮንን ባዘዘው መሠረት ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የሥራ ድርሻቸው ክፍፍል ይህ ነው። የሌዋውያን ስም ዝርዝር 20 የሌዊ ልጆች የቤተሰብ አለቆች የሆኑ ስማቸው ከዚህ በታች የተመለከተው ነው፦ ዬሕደያ በሸቡኤል በኩል የዓምራም ዘር ነው፤ 21 ዩሺያ የረሐብያ ዘር ነው፤ 22 ያሐት በሸሎሚት በኩል የይጽሃር ዘር ነው፤ 23 ይሪያ፥ አማርያ፥ ያሕዚኤልና ይቃምዓም የኬብሮን ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ስማቸው የተመዘገበው በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ነው። 24 ሻሚር በሚካ በኩል የዑዚኤል ዘር ነው፤ 25 ዘካርያስ በሚካ ወንድም በዩሺያ በኩል የዑዚኤል ዘር ነው፤ 26 ማሕሊ፥ ሙሺና ያዕዚያ የመራሪ ዘሮች ናቸው፤ 27 ያዕዚያም ሾሃም፥ ዛኩርና ዒብሪ ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 28-29 ማሕሊም አልዓዛርና ቂሽ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ አልዓዛር አንድም ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ቂሽ ግን ይራሕመኤል ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ነበረው። 30 የሙሺም ልጆች፥ ማሕሊ፥ ዔዴርና ያሪሞት ነበሩ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የሌዊ ዘር ቤተሰቦች ናቸው። 31 የእያንዳንዱ ቤተሰብ አለቃና ታናሹ እንደ ታላቁ በእኩልነት ልክ ዘመዶቻቸው የአሮን ልጆች የነበሩት ካህናት ያደርጉት በነበረው ዐይነት ለሥራቸው ምድብ ዕጣ ይጥሉ ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት፥ ሳዶቅ፥ አቤሜሌክና የካህናትና የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ሁሉ በተገኙበት ዕጣ ተጣጥለዋል። |