Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ዳዊት በጣም በሸመገለ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው።


የሌዋውያን አገልግሎት

2 ንጉሥ ዳዊት የእስራኤልን አለቆች እንዲሁም ካህናትንና ሌዋውያንን በሙሉ በአንድነት ሰበሰበ፤

3 ዕድሜአቸው ሠላሳና ከዚያም በላይ የሆኑትን ሌዋውያን ወንዶችን ቈጠረ፤ ጠቅላላ ድምራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ሆነ፤

4 ንጉሡ ከእነርሱ ኻያ አራት ሺህ የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን የቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ መደባቸው፤ ስድስት ሺህ የሚሆኑትን ባለሥልጣኖችና ዳኞች ሆነው እንዲሠሩ መደባቸው።

5 አራት ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ለዘብ ጥበቃ ተመደቡ፤ ሌሎች አራት ሺህ ደግሞ ንጉሡ በሚሰጣቸው የሙዚቃ መሣሪያ እግዚአብሔርን በዝማሬ ለማመስገን ተመደቡ።

6 ዳዊት ሌዋውያንን በየጐሣቸው ክፍል መሠረት በሦስት ቦታ መደባቸው፤ እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ተብለው የሚጠሩት ናቸው።

7 ጌርሾን ላዕዳንና ሺምዒ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤

8 ላዕዳንም ይሒኤል፥ ዜታምና ኢዮኤል ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤

9 ሺምዒም ሸሎሞት፥ ሐዚኤልና ሃራን ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፥ እነዚህ ሁሉ የላዕዳን ዘሮች ለሆኑት ጐሣዎች አለቆች ነበሩ፤

10-11 ሺምዒም በዕድሜአቸው ተራ ያሐት፥ ዚዛ፥ ይዑሽና በሪያ ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ያሖት የመጀመሪያው፥ ዚዛ ሁለተኛው ነበሩ፤ ይዑሽና በሪያ ብዙ ልጆች ስላልነበሩአቸው እንደ አንድ ጐሣ ይቈጠሩ ነበር።

12 ቀዓትም ዓምራም፥ ዩጺሃር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤

13 የቀዓት የበኲር ልጅ ዓምራም፥ የአሮንና የሙሴ አባት ነበር፤ አሮንና ዘሮቹ ለዘለቄታው ለንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች እንዲሆኑ፥ እግዚአብሔርን በማምለክ ሥነ ሥርዓት ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ፥ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉና በስሙም ሕዝቡን እንዲባርኩ ተለይተው ነበር፤

14 የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ልጆች ቊጥራቸው ከሌዋውያን ጋር ነበር።

15 ሙሴም ጌርሾምና ኤሊዔዘር ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤

16 ከጌርሾም ወንዶች ልጆች መካከል መሪው ሸቡኤል ነበር፤

17 ኤሊዔዘርም ረሐብያ ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ነበረው፤ ረሐብያ ግን ብዙ ዘሮች ነበሩት።

18 የቀዓት ሁለተኛ ልጅ ይጽሐር የጐሣው አለቃ የነበረ ሸሎሚት ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ነበረው፤

19 የኬብሮንም ልጆች አለቃ ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው ያሕዚኤልና አራተኛው ይቃምዓም ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

20 አራተኛ የዑዚኤልም ልጆች አለቃ ሚካ፥ ሁለተኛው ዩሺያ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

21 መራሪም ማሕሊና ሙሺ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ማሕሊም አልዓዛርና ቂሽ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

22 አልዓዛር ግን ከሴቶች በቀር አንድም ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ የእርሱ ሴቶች ልጆች የአጐታቸውን የቂሽን ወንዶች ልጆች አገቡ፤

23 የመራሪ ሁለተኛ ልጅ ሙሺም ማሕሊ ዔዴርና ይሬሞት ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

24 እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተሰባቸው የተዘረዘሩት የሌዊ ዘሮች ሲሆኑ፥ እያንዳንዳቸው በየስማቸው ተጠቅሰዋል። ኻያ ዓመት የሞላው ወይም ከዚያ በላይ የሆነው እያንዳንዱ የሌዊ ዘር በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ባለው ሥራ ድርሻ ነበረው።

25 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሰላምን ሰጥቶአል፤ ከዚህም በላይ እርሱ ራሱ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል፤

26 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ሌዋውያን መሸከም አይኖርባቸውም።”

27 ዳዊት ለመጨረሻ ጊዜ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያን ሁሉ ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ ተመዘገቡ፤

28 ኀላፊነታቸውም የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በሚያከናውኑት ተግባር መርዳት፥ የአደባባዩንና የክፍሎቹን እንክብካቤ መጠበቅ፥ ንዋያተ ቅድሳትን ማንጻት፥ እንዲሁም አጠቃላይ የሆነውን የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ማከናወን ነው።

29 ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ ለሚቀርበው ኅብስትና ዱቄት፥ ያለ እርሾ ለሚጋገረው ቂጣና በወይራ ዘይት ለሚለወሰው ዱቄት ኀላፊዎች ሲሆኑ፥ ለቤተ መቅደስ መባ ሆኖ የሚቀርበውን ሁሉ የሚመዝኑና የሚለኩ እነርሱ ነበሩ፤

30-31 ዘወትር ጠዋትና ማታ፥ እንዲሁም ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የሚቀርበው ነገር በሚቃጠልበት በየሰንበቱ፥ በየወሩ መባቻና በሌሎችም በዓላት እግዚአብሔርን ማመስገንና ማክበር የእነርሱ ተግባር ነበር፤ በየጊዜው ይህን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሌዋውያን ቊጥራቸው ምን ያኽል መሆን እንደሚገባው ደንቦች ነበሩ፤ ሌዋውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ለሁልጊዜ ተመድበዋል።

32 እንዲሁም እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና ቤተ መቅደሱን የመንከባከብ ኀላፊነት የእነርሱ ነበር፤ በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚፈጸመው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ዘመዶቻቸውን የአሮን ዘሮች የሆኑ ካህናትን ይረዱ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告