Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ዳዊትም “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ ሊኖሩ የሚገባቸው በዚህ ስፍራ ነው” አለ።


ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት

2 ንጉሥ ዳዊት በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን መጻተኞች በአንድነት ሰብስቦ በሥራ ላይ እንዲሰማሩ አደረገ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ እንዲሆን ድንጋይ ጠራቢዎችን መደበ፤

3 ዳዊት ለቅጽር በሮቹ መሥሪያ የሚሆን ምስማርና ማጠፊያ የሚሠራበት ብዙ ብረት፥ እንዲሁም የክብደቱ ሚዛን እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ አዘጋጀ፤

4 የጢሮስና የሲዶን ሕዝብ ቊጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ የሊባኖስ ዛፍ ግንድ እንዲያመጡለት አደረገ።

5 ዳዊት “ልጄ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሚሠራው ቤተ መቅደስ እጅግ የተዋበና በዓለም ዝነኛ መሆን ይገባዋል፤ ነገር ግን እርሱ ገና ልጅና በዕውቀትም ያልበሰለ በመሆኑ፥ እኔ ሁሉን ነገር አዘጋጅለታለሁ” ሲል በልቡ አሰበ፤ ስለዚህም ዳዊት ከመሞቱ በፊት ብዙ የቤት መሥሪያ ዕቃዎችን አዘጋጀ።

6 ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን አስጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲሠራ አዘዘው፤

7 እንዲህም አለው፤ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቤ አስቤ ነበር፤

8 እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ብዙ ሰው ገድለሃል፤ በብዙ ጦርነቶችም ላይ ውጊያ አድርገሃል፤ ብዙ ደም በማፍሰስህም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አልፈቅድልህም’ ብሎኛል፤

9 ይሁን እንጂ እንዲህ በማለት የተስፋ ቃል ሰጥቶኛል፥ ‘እኔ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፌ ሰላም ስለምሰጠው በሰላም የሚያስተዳድር ወንድ ልጅ ይኖርሃል፤ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ለእስራኤል ሰላምና ጸጥታ ስለምሰጥ ስሙ ሰሎሞን ተብሎ ይጠራል፤

10 ለእኔ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ እርሱ ነው፤ እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ መንግሥቱም በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።’ ”

11 ዳዊት ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለእርሱ ቤተ መቅደስ ትሠራለት ዘንድ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ሁሉን ነገር ያከናውንልህ፤

12 በእስራኤል ላይ ሥልጣን በሚሰጥህ ጊዜ ያምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጥህ፤

13 እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጎችንና ሥርዓቶችን ሁሉ ብትፈጽም፥ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ በርታ፤ ቈራጥ ሁን፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ።

14 ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ የሆነ እንደሆን፥ በበኩሌ ለሕንጻ ሥራ የሚውል ሦስት ሺህ አራት መቶ ቶን ወርቅና ከሠላሳ አራት ሺህ ቶን በላይ የሚሆን ብር አከማችቼልሃለሁ፤ በተጨማሪም ስፍር ቊጥር የሌለው ነሐስና ብረት አዘጋጅቼልሃለሁ፤ እንዲሁም እንጨትና ድንጋይ አዘጋጅቼልሃለሁ፤ ይሁን እንጂ አንተም በተጨማሪ ማግኘት አለብህ፤

15 አንተ ብዙ ሠራተኞች ድንጋይ የሚፈልጡ፥ ግንበኞችና አናጢዎች፥ እንዲሁም ባለሙያዎች በየዐይነቱ አሉልህ፤

16 በወርቅ፥ በብር፥ በነሐስና በብረት ሥራ የታወቁ ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ሰዎች አሉህ፤ እንግዲህ አሁን ሥራህን ጀምር፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።”

17 ዳዊት የእስራኤል መሪዎች በሙሉ ልጁን ሰሎሞንን ይረዱት ዘንድ ትእዛዝ በመስጠት እንዲህ አላቸው፤

18 “አምላካችሁ እግዚአብሔር እስከ አሁን ከእናንተ ጋር አይደለምን? በሁሉም አቅጣጫ ሰላምን ሰጥቶአችሁ የለምን? በዚህች ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች ሁሉ ድል አድርጌ እንድይዛቸው ፈቅዶልኛል፤ እነርሱም ለእናንተና ለእግዚአብሔር ተገዢዎች ሆነዋል፤

19 እንግዲህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ አገልግሉ፤ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦትና እግዚአብሔርን ለማምለክ መገልገያ የሆኑትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥታችሁ በውስጡ ማኖር ትችሉ ዘንድ ቤተ መቅደሱን ለክብሩ መሥራት ጀምሩ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告