Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት የሕዝብ ቈጠራ ማድረጉ
( 2ሳሙ. 24፥1-25 )

1 ሰይጣን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተነሥቶ ዳዊትን የሕዝብ ቈጠራ እንዲያደርግ አነሣሣው።

2 ዳዊት ለኢዮአብና ለሌሎቹ የጦር መኰንኖች “በመላው እስራኤል ከአገሪቱ ዳር እስከ ዳር፥ ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ሄዳችሁ ሕዝቡን ቊጠሩ፤ እኔ በእስራኤል ምን ያኽል ሕዝብ እንዳለ ማወቅ እፈልጋለሁ” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።

3 ኢዮአብም “ንጉሥ ሆይ፥ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ አሁን ካሉት ይልቅ በመቶ እጅ ያብዛልህ! እነርሱ በሙሉ የአንተ አገልጋዮች ናቸው፤ ታዲያ አንተ የሕዝብ ቈጠራ በማድረግ ሕዝቡን በሙሉ በደለኛ ለምን ታደርጋለህ?” አለ።

4 ንጉሡ ግን ትእዛዙን እንዲፈጽም ኢዮአብን አስገደደው፤ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ ሕዝቡንም ለመቊጠር በአገሪቱ በሙሉ ተዘዋውሮ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

5 ለውትድርና አገልግሎት ብቁ የሆኑትን ሰዎች ጠቅላላ ድምር ለዳዊት አስታወቀ፤ እነርሱም ከእስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሲሆኑ፥ ከይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺህ ነበሩ፤

6 ኢዮአብ በዚህ በንጉሡ ትእዛዝ ያልተስማማ በመሆኑ፥ የሌዊንና የብንያምን ነገዶች አልቈጠረም።

7 እግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ እጅግ ስለ ተቈጣ እስራኤልን ቀጣ።

8 ዳዊትም እግዚአብሔርን “እኔ ይህን በማድረጌ እጅግ ከባድ የሆነ ኃጢአት ሠርቼአለሁ! እባክህ ምሕረት አድርግልኝ፤ የስንፍና ሥራ ፈጽሜአለሁ!” አለው።

9 በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የዳዊት ነቢይ የሆነውን ጋድን እንዲህ አለው፤

10 “ሄደህ ዳዊትን ‘እነሆ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ እኔም አንተ የምትመርጠውን አደርጋለሁ’ ይላል” ብለህ ንገረው።

11 ጋድም ወደ ዳዊት ሄዶ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረውን ሁሉ ገለጠለት፤ እንዲህም ሲል ጠየቀው፤

12 “በምድርህ ላይ ሦስት ዓመት ራብ ከሚሆን ወይም ሦስት ወር ጠላቶችህ ከሚያሳድዱህ ወይም እግዚአብሔር በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን በሰይፍ ከሚመታህና ቸነፈር በምድሪቱ ላይ አምጥቶ በእስራኤል ምድር ሁሉ በሞት የሚቀሥፍ መልአክ ከሚልክብህ የትኛውን ትመርጣለህ? እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበውን መልስ ስጠኝ።”

13 ዳዊትም “እነሆ እኔ ለምርጫ በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ ነኝ! ይሁን እንጂ በሰው እጅ መውደቅ አልፈልግም፤ እግዚአብሔር መሐሪ ስለ ሆነ እርሱ ራሱ ይቅጣኝ” ሲል መለሰ።

14 ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ቸነፈር አመጣ፤ ከሕዝቡም ሰባ ሺህ የሚሆኑት አለቁ፤

15 ቀጥሎም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ መልአክ ልኮ ነበር፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ማጥፋት እንደ ጀመረ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያደረሰው ችግር አሳዝኖት መልአኩን “እስከ አሁን የደረሰባቸው ችግር ይበቃልና አቁም!” አለው። በዚያን ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

16 ዳዊትም መልአኩ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ሰይፉን በእጁ እንደ ያዘ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ አየው፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ማቅ ለብሰው የነበሩት የሕዝቡ አለቆች በሙሉ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ።

17 ዳዊትም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በደል የፈጸምኩት እኔ ነኝ፤ ሕዝቡ እንዲቈጠር ትእዛዝ ያስተላለፍኩትም እኔ ነኝ፤ ታዲያ እነዚህ አሳዛኝ ሕዝብህ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እኔንና ቤተሰቤን ቅጣ እንጂ በሕዝብህ ላይ ይህንን መቅሠፍት አታውርድ።”

18 የእግዚአብሔር መልአክ ጋድን “ዳዊት ወደ ኢያቡሳዊው ወደ ኦርና አውድማ ሄዶ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንዲሠራ ንገረው” አለው፤

19 ዳዊትም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመፈጸም ጋድ እንደ ነገረው ለማድረግ ሄደ፤

20 በዚያም አውድማ ላይ ራሱ ኦርናና አራት ወንዶች ልጆቹ ስንዴ ይወቁ ነበር፤ መልአኩንም ባዩ ጊዜ ልጆቹ ሮጠው ተደበቁ።

21 ኦርናም ዳዊት ወደ እነርሱ እየቀረበ መምጣቱን ባየ ጊዜ ከአውድማው ወጥቶ ወደ መሬት ለጥ በማለት እጅ ነሣ፤

22 ዳዊትም “ቸነፈሩ ይወገድ ዘንድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንድሠራበት አውድማህን ሽጥልኝ፤ እኔም ሙሉ ዋጋ እሰጥሃለሁ” አለው።

23 ኦርናም “ንጉሥ ሆይ፥ ውሰደው፤ የፈለግኸውንም አድርግበት፤ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ሆነው እንዲቃጠሉ እነዚህን በሬዎች ጨምረህ ውሰድ፤ እነዚህም የእህል መውቂያ እንጨቶች ለማገዶ ይሁኑልህ፤ ስንዴውንም መባ አድርገህ አቅርበው፤ እነሆ ሁሉንም ለአንተ ሰጥቼሃለሁ” አለው።

24 ንጉሥ ዳዊት ግን “ይህስ አይሆንም፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ፤ የአንተ ንብረት የሆነውን፥ እኔ ምንም ዋጋ ያልከፈልኩበትን ነገር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጌ ማቅረብ አልፈልግም” ሲል መለሰለት።

25 ለኦርናም የአውድማውን ሒሳብ ስድስት መቶ ከወርቅ የተሠራ ገንዘብ ሰጠው፤

26 ዳዊት በዚያ ስፍራ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ በጸለየም ጊዜ እግዚአብሔር በመሠዊያው ላይ የነበረውን መሥዋዕት የሚበላ እሳት ከሰማይ በመላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጠው።

27 እግዚአብሔርም መልአኩን “ሰይፍህን ወደ አፎቱ መልስ” አለው፤ መልአኩም እንደታዘዘው አደረገ፤

28 በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ጸሎቱን የሰማለት መሆኑን ዳዊት ተገነዘበ፤ ስለዚህም በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በሚገኘው መሠዊያ ላይ እንደገና መሥዋዕት አቀረበ፤

29 ሙሴ በበረሓ የሠራው እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳንና መሥዋዕት ይቀርብበት የነበረው መሠዊያ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በገባዖን በሚገኘው የማምለኪያ ስፍራ ይገኛሉ፤

30 ነገር ግን ዳዊት የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ ወደዚያ ሄዶ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አልቻለም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告