1 ዜና መዋዕል 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት ራባ ተብላ የምትጠራውን ከተማ በድል አድራጊነት መያዙ ( 2ሳሙ. 12፥26-31 ) 1 በተከታዩ የዓመት መባቻ ማለትም ነገሥታት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጦርነት በሚሄዱበት ወራት፥ ኢዮአብ ሠራዊቱን እየመራ ሄዶ የዐሞንን አገር ወረረ፤ ንጉሥ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ የኢዮአብ ሠራዊትም የራባን ከተማ ከበው አደጋ በመጣል ደመሰሱአት፤ 2 ሚልኮም ተብሎ የሚጠራው የዐሞናውያን ጣዖት ሠላሳ አራት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ዘውድ ነበረው፤ በውስጡም የከበረ ዕንቊ ነበር፤ ዳዊት ያንን ዘውድ ወስዶ በራሱ ላይ ደፋ፤ እንዲሁም ከከተማይቱ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ 3 የከተማይቱንም ሕዝብ ማርኮ በመጋዝ፥ በዶማና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ በዐሞን በሚገኙ በሌሎች ታናናሽ ከተማዎች የሚኖሩትንም ሰዎች በዚሁ ዐይነት እንዲሠሩ አደረገ፤ ከዚያም በኋላ እርሱና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በፍልስጥኤማውያን ኀያላን ሰዎች ላይ የተደረገ ጦርነት ( 2ሳሙ. 21፥15-22 ) 4 ዘግየት ብሎም በጌዜር የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ላይ ጦርነት ተደረገ፤ በዚያን ጊዜ የሑሻ ተወላጅ የሆነው ሲበካይ፥ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፓይ ተብሎ የሚጠራውን ኀያል ሰው ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሸነፉ። 5 በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ሌላም ጦርነት ነበረ፤ በዚያን ጊዜ የያዒር ልጅ ኤልሐናን የጋት ተወላጅ የሆነውን የጦሩ እጀታ ውፍረቱ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጎልያድን ወንድም ላሕሚን ገደለ። 6 ሌላም ጦርነት በጋት ተደረገ፤ በዚያም ጦርነት በእያንዳንዱ እጅና በእያንዳንዱ እግር ላይ ስድስት ስድስት በጠቅላላ ኻያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበር፤ እርሱም ኀያላን ከሆኑት ከራፋይም ዘር ነበር፤ 7 ይህም ሰው እስራኤላውያንን ተገዳደረ፤ እርሱንም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናታን ገደለው። 8 በዳዊትና በሠራዊቱ የተገደሉት እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ኀያላን ከሆኑት የራፋይም ዘር ነበሩ። |