1 ዜና መዋዕል 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይሁዳ ትውልድ 1 ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ 2 ዳን፥ ዮሴፍ፥ ብንያም፥ ንፍታሌም፥ ጋድና አሴር ናቸው። 3 ይሁዳ ከከነዓናዊት ሚስቱ ከባትሹዓ ዔር፥ ኦናንና ሼላ ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ የበኲር ልጁ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሰው ስለ ነበር እግዚአብሔር በሞት ስለ ቀሠፈው፥ 4 ይሁዳ የልጁ ሚስት ከነበረችው ከትዕማር ፋሬስና ዛራሕ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። የይሁዳ ልጆች በድምሩ አምስት ነበሩ። 5 ፋሬስም ሔጽሮንና ሐሙል የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 6 የእርሱም ወንድም ዛራሕ አምስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ዚምሪ፥ ኤታን፥ ሄማን፥ ካልኮልና ዳርዳዕ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 7 ከዛራሕ ትውልድ አንዱ የሆነው የካርሚ ልጅ ዓካን ለእግዚአብሔር ከተለየው ምርኮ በስርቆት ወስዶ በመደበቁ ምክንያት በእስራኤል ሕዝብ ላይ መቅሠፍት አምጥቶ ነበር። 8 ኤታንም ዐዛርያ የተባለ አንድ ወንድ ልጅ ወለደ። የንጉሥ ዳዊት የትውልድ ሐረግ 9 ሔጽሮን ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ይራሕመኤል፥ ራምና ካሌብ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፤ 10 አራም የአሚናዳብ አባት ነበር፤ አሚናዳብም የይሁዳ ልጆች አለቃ የሆነው ነአሶንን ወለደ። 11 ነአሶን ሳልሞንን ወለደ፤ ሳልሞንም ቦዔዝን ወለደ። 12 ቦዔዝ ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ። 13 እሴይ የበኲር ልጁን ኤሊአብንና ሁለተኛውን አሚናዳብን፥ ሦስተኛውን ሻማን፥ 14 አራተኛውን ናትናኤልን አምስተኛውን ራዳይን፥ 15 ስድስተኛውን ኦጼምና ሰባተኛውን ዳዊትን ወለደ። 16 እኅቶቻቸውም ጽሩያና አቢጌል ይባሉ ነበር፤ የጽሩያም ሦስት ወንዶች ልጆች አቢሳይ፥ ኢዮአብና ዓሣሄል ተብለው ይጠሩ ነበር። 17 ሌላይቱ የእሴይ ሴት ልጅ አቢጌል የእስማኤል ዘር የሆነውን ዬቴርን አግብታ ዐማሣ ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደች። የሔጽሮን ትውልድ 18 የሔጽሮን ልጅ ካሌብ ዐዙባ የተባለች ሴት አግብቶ ይሪዖት ተብላ የምትጠራ ሴት ልጅ ወለደ፤ ይሪዖትም ዬሼር፥ ሾባብና አርዶን ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደች። 19 ዐዙባ ከሞተችም በኋላ ካሌብ ኤፍራታ ተብላ የምትጠራ ሴት አግብቶ ሑር ተብሎ የሚጠራ ወንድ ልጅ ወለደ፤ 20 ሑርም ኡሪ የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ኡሪም ባጽልኤል ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደ። 21 ሔጽሮን ሥልሳ ዓመት ሲሞላው የገለዓድ እኅት የነበረችውን የማኪርን ልጅ አግብቶ ሰጉብ የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ 22 ሰጉብም ያኢር ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ያኢር በገለዓድ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን ኻያ ሦስት ከተሞች ይገዛ ነበር፤ 23 ነገር ግን የገሹርና የአራም ነገሥታት ሥልሳ የሚያኽሉ ታናናሽ ከተሞችን ከዚያው ከገለዓድ ድል አድርጎ ያዘ፤ ይህም የያኢርንና የቀናትን መንደሮች እንዲሁም በአቅራቢያቸው ያሉትንም ታናናሽ ከተሞች የሚያጠቃልል ነበር፤ በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የገለዓድ አባት የማኪር ዘሮች ናቸው፤ 24 ከሔጽሮን በካሌብ ኤፍራታ ከሞተ በኋላ ሚስቱ አብያ አሽሑር የተባለውን ልጁን ወለደችለት አሽሑርም የተቆዓ አባት ነው። የይራሕመኤል ትውልድ 25 የሔጽሮን የበኲር ልጅ ይራሕመኤል አምስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም የመጀመሪያው ራም ቀጥሎም ቡና፥ ኦሬን፥ ኦጼምና አሒያ ተብለው የሚጠሩ ነበሩ፤ 26-27 ራም ሦስት ወንድ ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ማዓጽ፥ ያሚንና ዔቄር ተብለው የሚጠሩ ናቸው፤ ይራሕመኤል፥ ዐታራ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሌላ ሴት አግብቶ ኦናም ተብሎ የሚጠራ ወንድ ልጅ ወለደ፤ 28 ኦናምም ሻማይና ያዳዕ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ሻማይም ናዳብና አቢሹር የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። 29 አቢሹርም አቢኃይል ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት አግብቶ አሕባንና ሞሊድ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 30 ናዳብ ሴሌድና አፋይም የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ሴሌድ ግን አንድም ልጅ ሳይወልድ ሞተ። 31 አፋይምም ዩሺዒ የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ዩሺዒም ሼሻን የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ። ሼሻንም አሕላይ የተባለውን ወንድ ልጅ ወለደ። 32 የሻማይ ወንድም ያዳዕ ዬቴርና ዮናታን ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ዬቴር ግን አንድም ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 33 ዮናታንም ፔሌትና ዛዛ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የይራሕመኤል ዘሮች ናቸው። 34 ኤሻን ከሴቶች በቀር ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ እርሱም ያርሐዕ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግብጻዊ አገልጋይ ነበረው፤ 35 ለዚህም ለአገልጋዩ ከሴቶች ልጆቹ አንዲቱን ዳረለት፤ ያርሐዕምም ዓታይ ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ወለደ፤ 36 ከዓታይ እስከ ኤሊሻማዕ ያለው የትውልድ ሐረግ፥ ኢታይ፥ ናታን፥ ዛባድ፥ 37 ኤፍላል፥ ዖቤድ፥ 38 ኢዩ፥ ዐዛርያ፥ 39 ሔሌጽ፥ ኤልዓሳ፥ 40 ሲስማይ፥ ሻሉም፥ 41 ይቃምያና ኤሊሻማዕ ነው። ሌሎቹ የካሌብ ትውልድ 42 የይራሕመኤል ወንድም የነበረው የካሌብ በኲር ልጅ ስሙ ሜሻዕ ይባል ነበር፤ ይህም ሜሻዕ ዚፍ ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደ፤ ዚፍም ማሬሻን ወለደ፤ ማሬሻም ኬብሮንን ወለደ፤ 43 ኬብሮንም ቆሬ፥ ታፑሐ፥ ሬቄምና ሼማዕ ተብለው የሚጠሩትን አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ። 44 ሼማዕም ራሐምን ወለደ፤ ራሐምም ዮርቀዓምን ወለደ፤ የሼማዕ ወንድም ሬቄም ሻማይን ወለደ፤ 45 ሻማይም ማዖንን ወለደ፤ ማዖንም ቤትጹርን ወለደ። 46 ካሌብ ዔፋ ተብላ የምትጠራ ቊባት ነበረችው፤ ከእርስዋም ሐራን፥ ሞጻና ጋዜዝ ተብለው የሚጠሩ ሌሎች ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ ሐራንም ጋዜዝ ተብሎ የሚጠራ ሌላም ወንድ ልጅ ወለደ። 47 ያህዳይ የተባለውም ሰው ሬጌም፥ ዮታም፥ ጌሻን፥ ፔሌጥ፥ ዔፋና ሻዓፍ ተብለው የሚጠሩ ስድስት ወንዶች ልጆችን ወለደ። 48 ካሌብ፥ ማዕካ የተባለች አንዲት ሌላ ቊባት ነበረችው፤ ከእርስዋም ሼቤርና ቲርሐና ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ 49 ይህችው ሴት ዘግየት ብላ ሌሎች ሁለት ወንዶች ልጆችን እነርሱም የማድማናን አባት ሳፋንና የማክቢናና የጊብዓን አባት ሻዋን ወለደችለት። ካሌብ በተጨማሪ ዓክሳ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ልጅ ነበረችው። 50 ከዚህ የሚከተሉትም የካሌብ ዘሮች ናቸው፦ ሑር የካሌብ ከሚስቱ ከኤፍራታ የተወለደው የመጀመሪያው ልጁ ሲሆን የሑር ልጅ የቂርያትይዓሪም አባት ሾባል ነው፤ 51 የሑር ሁለተኛው ልጅ ሳልማ ደግሞ የቤተልሔም አባት፥ የሑር ሦስተኛ ልጅ ሐሬፍ የቤት ጋዴር አባት ነው። 52 የቂርያትይዓሪም አባት ሾባል ሌሎችም ልጆች ነበሩት፦ እነርሱም ሔሮኤትና የመኑሖት ጐሣዎች እኩሌታ ነበሩ። 53 እንዲሁም የቂርያትይዓሪም ቤተሰቦች ዩትራውያን፥ ፑታውያን፥ ሹማታውያንና ሚሽራዓውያን ተብለው የሚጠሩ ነበሩ፤ ከእነርሱም የጾርዓና የኤሽታኦል ትውልድ ተገኙ። 54 የሳልማ ልጆች ቤተልሔም፥ ነጦፋውያን፥ ዐጣሮት ቤት ዮአብ፥ የመናሐታውያን እኩሌታና ጾርዓውያን ነበሩ። 55 ቲርዓውያን፥ ሺምዓውያንና ሱካውያን የተባሉት ታሪክ በመጻፍና በመገልበጥ ጥበበኞች የነበሩት ጐሣዎች ያዕቤጽ ተብላ በምትጠራ ትንሽ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ እነርሱም ከሬካባውያን አባት ከሐሜት የወጡ ቄናውያን ነበሩ። |