1 ዜና መዋዕል 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት ዐሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል ማድረጉ ( 2ሳሙ. 10፥1-19 ) 1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዐሞን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሐኑን ነገሠ፤ 2 ንጉሥ ዳዊትም “አባቱ ናዖስ ለእኔ እንዳደረገልኝ ሁሉ፥ እኔም ለልጁ ለሐኑን ታማኝ ወዳጅ በመሆን ወሮታውን እከፍላለሁ” አለ፤ ስለዚህም ዳዊት የሐዘን ተካፋይነቱን ለመግለጥ መልእክተኞች ላከ። መልእክተኞቹም ሊያጽናኑት ወደ ዐሞን ምድር በደረሱ ጊዜ፥ 3 ዐሞናውያን ባለሥልጣኖች ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ዳዊት እነዚህን ሰዎች የላከው አባትህን በማክበር የሐዘንህ ተካፋይ ለመሆን ይመስልሃልን? ከቶ እንዳይመስልህ! እርሱ እነዚህን መልእክተኞች የላከው ምድሪቱን ወሮ መያዝ ይችል ዘንድ እንዲሰልሉለት ነው።” 4 ስለዚህ ሐኑን የዳዊትን መልእክተኞች ይዞ ጢማቸውን ላጨ፤ ኀፍረተ ሥጋቸው እስኪታይ ድረስ ከወገባቸው በታች ያለውን ልብስ ቈረጠና ወደ አገራቸው ሰደዳቸው፤ 5 እነርሱም ወደ ቤታቸው ለመመለስ አፈሩ፤ ዳዊት ስለ ሆነው ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ መልእክተኞች ልኮ በኢያሪኮ እንዲቈዩና ጢማቸው እስከሚያድግ ድረስ እንዳይመለሱ ነገራቸው። 6 ዐሞናውያን በገዛ እጃቸው ዳዊትን ጠላት እንዳደረጉት ተገነዘቡ፤ ስለዚህም ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር ከፍለው ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ከላይኛው መስጴጦምያና የሶርያ ግዛቶች ከሆኑት ከማዕካና ከጾባ ተከራዩ፤ 7 የተከራዩአቸው ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠረገሎችና የንጉሥ ማዕካ ሠራዊት መጥተው በሜዳባ አጠገብ ሰፈሩ፤ ዐሞናውያንም ከየከተሞቻቸው ወጥተው ለጦርነት ተዘጋጁ። 8 ዳዊት ስለዚህ ጉዳይ ሰምቶ ከመላው ሠራዊት ጋር ኢዮአብን በእነርሱ ላይ አዘመተ፤ 9 ዐሞናውያንም ተሰልፈው መጥተው የእነርሱ ዋና ከተማ በሆነችው በራባ መግቢያ በር አጠገብ ስፍራቸውን ያዙ፤ እነርሱን ሊረዱ የመጡ ነገሥታትም ገላጣማ በሆነው ገጠር ስፍራቸውን ያዙ። 10 ኢዮአብ የጠላት ሠራዊት ከፊትና ከኋላ በኩል አደጋ እንደሚጥልበት ተመለከተ፤ ስለዚህ ከእስራኤል ወታደሮች ጀግኖች የሆኑትን መርጦ በሶርያውያን ሠራዊት ፊት ለፊት አቆማቸው። 11 ከሠራዊቱ ቀሪውን ክፍል በወንድሙ በአቢሳ ትእዛዝ ሥር አደረገ፤ አቢሳም እነርሱን በዐሞናውያን ፊት ለፊት አሰለፋቸው። 12 ኢዮአብም አቢሳን እንዲህ አለው፤ “ሶርያውያን ድል ሊያደርጉኝ መቃረባቸውን በምታይበት ጊዜ መጥተህ እርዳኝ፤ እኔም ዐሞናውያን አንተን ድል ሊያደርጉህ በሚቃረቡበት ጊዜ መጥቼ እረዳሃለሁ፤ 13 እንግዲህ አይዞህ በርታ! ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተማዎች ስንል በርትተን እንዋጋ፤ ለዚህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን።” 14 ኢዮአብና ሠራዊቱ አደጋ ለመጣል ወደፊት በገሠገሡ ጊዜ ሶርያውያን ሸሹ፤ 15 ዐሞናውያንም የሶርያውያንን መሸሽ ባዩ ጊዜ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማይቱ አፈገፈጉ፤ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 16 ሶርያውያን በእስራኤላውያን ድል እንደ ተመቱ በተገነዘቡ ጊዜ ከኤፍራጥስ በስተ ምሥራቅ በኩል ካሉት የሶርያ ግዛቶች ሠራዊት አስመጥተው በሾባክ አዛዥነት ሥር አደረጉአቸው፤ ሾባክ የጾባ ንጉሥ የሀዳድዔዜር የጦር አዛዥ ነበር፤ 17 ዳዊት ስለዚህ ነገር በሰማ ጊዜ የእስራኤላውያንን የጦር ኀይል ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ የውጊያ መስመሩን ያዘ፤ ሶርያውያንም እንደዚሁ ቦታቸውን ይዘው ከዳዊት ጋር ጦርነት ገጠሙ። 18 እስራኤላውያንም ሶርያውያንን ወደ ኋላ መልሰው አባረሩአቸው፤ ዳዊትና ሠራዊቱ ሰባት ሺህ ሠረገላ ነጂዎችን፥ አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮችን ገደሉ፤ እንዲሁም ሾባክ ተብሎ የሚጠራውን የሶርያውያንን የጦር አዛዥ ገደሉ፤ 19 በሀዳድዔዜር ሥልጣን ሥር የነበሩት ነገሥታት በእስራኤል ድል እንደ ተመቱ በተገነዘቡ ጊዜ ከዳዊት ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው የእርሱ ገባሮች ሆኑ፤ ከዚያን በኋላም ሶርያውያን ዐሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኞች አልሆኑም። |