1 ዜና መዋዕል 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት በጦርነት የተቀዳጃቸው ድሎች ( 2ሳሙ. 8፥1-18 ) 1 ጥቂት ዘግየት ብሎም ንጉሥ ዳዊት እንደገና በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ በመጣል ድል አደረጋቸው፤ አስገበራቸውም፤ የጋትን ከተማና በዙሪያዋ ያሉትን መንደሮች ከእነርሱ ቊጥጥር ነጻ አደረገ፤ 2 ሞአባውያንንም ድል ነሥቶ እንዲገብሩለት አደረገ። 3 ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት በሶርያ አገር እስከ ሐማት ግዛት አጠገብ በምትገኘው በጾባ ንጉሥ በሀዳድዔዜር ላይ አደጋ ጣለ፤ ይህንንም ያደረገው ሀዳድዔዜር ከላይ በኩል በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዘምቶ ስለ ነበር ነው፤ 4 ዳዊት የሀዳድዔዜርን አንድ ሺህ ሠረገሎች፥ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ኻያ ሺህ እግረኛ ሠራዊት ማረከ፤ አንድ መቶ ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶችን ለራሱ አስቀርቶ የቀሩትን ፈረሶች ቋንጃ ቈረጠ። 5 በደማስቆ ያሉ ሶርያውያን የጾባን ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት ሠራዊት በላኩ ጊዜ ዳዊት በእነርሱም ላይ አደጋ ጥሎ ኻያ ሁለት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ 6 ከዚያም በኋላ በግዛታቸው ላይ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሕዝቡም ግብር እየከፈለ ለእርሱ ተገዛ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በየስፍራው ድል አድራጊ አደረገው፤ 7 ዳዊት የሀዳድዔዜር ባለሟሎች የሆኑ ባለሥልጣኖች አንግበውት የነበረውን ከወርቅ የተሠራ ጋሻ ሁሉ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ 8 እንዲሁም የሀዳድዔዜር ግዛት ከነበሩት ከጢብሐትና ከኩን ከተማዎች እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ ወሰደ፤ ዘግየት ብሎም ሰሎሞን በነሐሱ የቤተ መቅደሱን ገንዳ፥ ዐምዶችና የነሐስ ዕቃዎች አሠራበት። 9 የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት የጾባን ንጉሥ የሀዳድዔዜርን መላ ሠራዊት ድል እንዳደረገ ሰምቶ 10 ቶዒ ከሀዳድዔዜር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት አድርጎ ስለ ነበር፥ ንጉሥ ዳዊትን እጅ እንዲነሣና በሀዳድዔዜር ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል ደስታውን እንዲገልጥለት ልጁን ዮራምን ወደ ዳዊት ላከ። ዮራምም ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ የተሠሩ ዕቃዎችን ገጸ በረከት አድርጎ ለዳዊት አመጣለት፤ 11 ንጉሥ ዳዊትም እነርሱን ወስዶ ከኤዶም፥ ከሞአብ፥ ከዐሞን፥ ከፍልስጥኤምና ከዐማሌቅ ሕዝቦች ማርኮ ካመጣቸው ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ ከተሠሩ ዕቃዎች ጋር ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት መገልገያ እንዲሆኑ አደረጋቸው። 12 የጸሩያ ልጅ አቢሳ ኤዶማውያንን በጨው ሸለቆ ውስጥ ድል አድርጎ ከእነርሱ መካከል ዐሥራ ስምንት ሺህ የሚሆኑትን ገደለ፤ 13 በመላው የኤዶም ግዛት ውስጥ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ በዚያም የሚኖሩ ሰዎች የንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በሁሉ ስፍራ ድል አድራጊ አደረገው። 14 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሕዝቡም ሁልጊዜ አድልዎ የሌለበት ፍትሕ እንዲያገኙ አደረገ። 15 የአቢሳ ወንድም ኢዮአብ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ የቤተ መዛግብት ኀላፊ ነበር፤ 16 የአሒጡብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ነበር፤ 17 የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ የንጉሥ ዳዊት ወንዶች ልጆች በአባታቸው መንግሥት ከፍተኛ ማዕርግ ነበራቸው። |