1 ዜና መዋዕል 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምናታን ለዳዊት የተናገረው ቃል ( 2ሳሙ. 7፥1-17 ) 1 ንጉሥ ዳዊት በዚህ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ነበር፤ አንድ ቀን ንጉሡ ነቢዩን ናታንን አስጠርቶ “እነሆ እኔ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጦአል!” አለው። 2 ናታንም “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። 3 ነገር ግን በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ናታንን እንዲህ አለው፤ 4 “ወደ አገልጋዬ ወደ ዳዊት ሄደህ እንዲህ በለው ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤ 5 የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ነጻ ካወጣሁበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖሬ አላውቅም፤ ዘወትር በድንኳን ውስጥ ሆኜ ከቦታ ወደ ቦታ እዘዋወር ነበር፤ 6 ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በተጓዝኩበት ዘመን ሁሉ እኔ ከሾምኳቸው መሪዎች መካከል አንዱን እንኳ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤተ መቅደስ እንዲሠራልኝ የጠየቅሁት አለን?’ 7 “ስለዚህ እኔ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ለአገልጋዬ ለዳዊት የምለውን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘ከበግ እረኝነት አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ 8 በሄድክበት ስፍራ ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርኩ፤ ጠላቶችህን ሁሉ ድል አደረግኹልህ፤ በዓለም ላይ እንዳሉት እንደታላላቅ ዝነኞች ሰዎች ስምህን ዝነኛ አደርገዋለሁ። 9-10 ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ እዚያም በገዛ ምድራቸው በሰላም እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ ግፈኞች እንደ ቀድሞው በፍጹም አያስጨንቁአቸውም፤ ከዚህ በፊት በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን እንደ ሾምኩበት ጊዜ ያለ ችግር ዳግመኛ አይደርስባቸውም፤ ጠላቶችህን ሁሉ አስገዛልሃለሁ፤ እኔ እግዚአብሔርም ንጉሣዊ ቤትህን እንደምሠራልህ እገልጥልሃለሁ። 11 ዕድሜህ ደርሶ ከአባቶችህ ጋር በሞት ስትቀላቀል፥ ከልጆችህ አንዱን አነግሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 12 ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝም እርሱ ይሆናል፤ ዙፋኑንም ለዘለዓለም የጸና እንዲሆን አደርጋለሁ፤ 13 እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ አንተ በሳኦል እግር ተተክተህ ትነግሥ ዘንድ ከዙፋኑ ባወረድኩት በሳኦል ላይ ባደረግሁት ዐይነት ምሕረቴን ከልጅህ በማራቅ አልተወውም። 14 በሕዝቤና በመንግሥቴ ላይ ለዘለዓለም እሾመዋለሁ፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ አይኖረውም።’ ” 15 በዚህ ዐይነት ናታን እግዚአብሔር የገለጠለትን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። ዳዊት ለእግዚአብሔር ያቀረበው የምስጋና ጸሎት ( 2ሳሙ. 7፥18-29 ) 16 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ድንኳን ሄደ፤ ተቀምጦም እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እኔ ይህን ሁሉ ነገር ታደርግልኝ ዘንድ እኔ ማነኝ? ቤተሰቤስ ምንድን ነው? 17 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ያለፈው ሁሉ በፊትህ የማይበቃ ሆኖ ስለ አገልጋይህ ቤት ለሚመጣው ሩቅ ዘመን አሁንም እንደገና እኔን እንደ ትልቅ ባለማዕርግ አድርገህ ተመለከትከኝ። 18 እንግዲህ ለአንተ ከዚህ በላይ ምን መናገር እችላለሁ? አንተ እኔን ታውቀኛለህ፤ ይሁን እንጂ ለእኔ ክብር ሰጥተኸኛል፤ 19 ይህን ታደርግልኝ ዘንድ እንዲሁም ወደፊት ታላቅ እንደምታደርገኝ ታስታውቀኝ ዘንድ በጎ ፈቃድህና ዕቅድህ ሆኖአል፤ 20 እግዚአብሔር ሆይ ከቶ አንተን የሚመስል ማንም የለም፤ እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21 ሕዝብህ እስራኤል ከየትኛው ሕዝብ ጋር ይነጻጸራል? አንተ እግዚአብሔር ከባርነት ነጻ አውጥተህ የራስህ ሕዝብ ያደረግኸው በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን? ሕዝብን ከግብጽ ለማስወጣት በመታደግህና በታላላቅ ሥራዎችህ ስምህን ታላቅና ገናና አደረግኸው። 22 እስራኤልን ዘለዓለም የራስህ ሕዝብ አደረግህ፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተም አምላካቸው ሆንክ። 23 “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ስለ እኔና ስለ ዘሮቼ የተናገርከውን የተስፋ ቃል ሁሉ ፈጽም፤ አደርጋለሁ ያልከውንም ሁሉ አድርግ፤ 24 ይህንንም የምታደርገው ስምህ ለዘለዓለም የገነነ ይሆን ዘንድና ሰዎችም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው እንዲሉ ነው፤ የእኔ የአገልጋይህ ቤትም በፊትህ የጸና ይሆናል። 25 አምላኬ ሆይ፥ አንተ ለእኔ ለባሪያህ ቤትን እንደምትሠራልኝ ስለ ገለጥክልኝ ይህን ጸሎት ለማቅረብ ድፍረት አገኘሁ። 26 እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ አምላክ ነህ፤ ይህንንም አስደናቂ የተስፋ ቃል ለእኔ ሰጥተኸኛል፤ 27 ስለዚህ በፊትህ ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ የእኔን የባሪያህን ቤት እንድትባርክ ፈቃድህ ይሁን፤ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ቤተሰቤን ባርከኸዋል፤ እርሱም ለዘለዓለም የተባረከ ይሆናል።” |