Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ የተደረገ ዝግጅት

1 ዳዊት የሚኖርባቸውን ቤቶች በራሱ ከተማ በኢየሩሳሌም ሠራ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት የሚኖርበትንም ስፍራ አዘጋጅቶ ድንኳን ተከለለት፤

2 ከዚህም በኋላ ዳዊት እግዚአብሔር ለዘለዓለም እርሱን እንዲያገለግሉና የቃል ኪዳኑንም ታቦት እንዲሸከሙ የመረጣቸው እነርሱን ስለ ሆነ “የቃል ኪዳኑን ታቦት መሸከም የሚገባቸው ሌዋውያን ብቻ ናቸው” አለ።

3 ስለዚህም ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደተዘጋጀለት ስፍራ ለመውሰድ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አስጠራ፤

4 ቀጥሎም የአሮንን ዘሮችና ሌዋውያንን አስጠራ፤

5 ከሌዋዊው ቀዓት ጐሣ፥ ኡሪኤል መቶ ኻያ ለሚሆኑት የጐሣው አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤

6 ከመራሪ ጐሣ፥ ዐሣያ ሁለት መቶ ኻያ ለሚሆኑት የጐሣው አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤

7 ከጌርሾን ጐሣ፥ ኢዮኤል መቶ ሠላሳ ለሚሆኑት የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤

8 ከኤሊጻፋን ጐሣ፥ ሸማዕያ ሁለት መቶ ለሚሆኑት የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤

9 ከኬብሮን ጐሣ፥ ኤሊኤል ሰማኒያ ለሚሆኑ የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤

10 ከዑዚኤል ጐሣ፥ ዓሚናዳብ መቶ ዐሥራ ሁለት ለሚሆኑ የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ።

11 ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲሁም ኡሪኤልን፥ ዐሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማዕያን፥ ኤሊኤልንና ዓሚናዳብን በአጠቃላይ ስድስት ሌዋውያንን ወደ ድንኳን ውስጥ አስገባ።

12 ሌዋውያኑንም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ እናንተ ለሌዋውያን ጐሣዎች መሪዎች ናችሁ፤ የእስራኤል አምላክን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት እኔ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ ተሸክማችሁ ታመጡ ዘንድ ራሳችሁንና ሌዋውያን ወገኖቻችሁን ሁሉ ቀድሱ፤

13 ከዚህ በፊት እናንተ ተገኝታችሁ ታቦቱን ባለመሸከማችሁ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ስላላገለገልነው አምላካችን እግዚአብሔር ቀጥቶናል።”

14 ከዚህ በኋላ የእስራኤል አምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው ይወስዱ ዘንድ ካህናትና ሌዋውያን ራሳቸውን አነጹ፤

15 እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሌዋውያን ታቦቱን በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎች ተሸክመው ሄዱ።

16 ዳዊት “በገና፥ መሰንቆና ጸናጽል በመሳሰሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ የደስታ መዝሙሮችን ይዘምሩ ዘንድ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን ሌዋውያንን ሹሙአቸው” በማለት የሌዋውያኑን መሪዎች ተናገረ፤

17-21 ከመዘምራን ጐሣ የነሐስ ጸናጽል የሚያንሿሹ የኢዮኤል ልጅ ሄማን፥ የእርሱ ዘመድ የሆነው የበራክያ ልጅ አሳፍ፥ እንዲሁም ከመራሪ ጐሣ የቁሳያ ልጅ ኤታን ተመረጡ፤ በከፍተኛ ድምፅ የሚደረደረውን በገና በመምታት የእነርሱ ረዳቶች እንዲሆኑም ዘካርያስ፥ ያዕዚኤል፥ ሸሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤሊአብ፥ ማዕሤያና በናያ ተመረጡ። በዝቅተኛ ድምፅ የሚደረደረውን በገና እንዲመቱ ማቲትያ፥ ኤሊፈሌ፥ ሚቅኔያ፥ ዐዛዝያ እንዲሁም ከቤተ መቅደስ ዘበኞች መካከል ዖቤድኤዶምና ዩዒኤል ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ተመረጡ።

22 ከናንያ የሙዚቃ ችሎታ ስለ ነበረው ለሌዋውያኑ መዘምራን መሪ ሆኖ ተመረጠ፤

23-24 በራክያ፥ ኤልቃና፥ ዖቤድኤዶምና ዩሒያ የቃል ኪዳኑ ታቦት ጠባቂዎች ሆነው ተመረጡ፤ ካህናቱ ሸባንያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዐማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያና ኤሊዔዘር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ፊት እየሄዱ እምቢልታ እንዲነፉ ተመረጡ።


የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱ
( 2ሳሙ. 6፥12-22 )

25 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት፥ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችና የጦር አዛዦች የቃል ኪዳኑን ታቦት ለማምጣት ወደ ዖቤድኤዶም ቤት ሄዱ፤ ከፍ ያለ የደስታ ሥነ ሥርዓትም አደረጉ፤

26 የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያን እግዚአብሔር ስለ ረዳቸው ሰባት ኰርማዎችንና ሰባት በጎችን ሠዉ፤

27 ዳዊት ከጥሩ በፍታ የተሠራ መጐናጸፊያና ኤፉድ ለብሶ ነበር፤ እንዲሁም መዘምራኑ በሙሉ፥ የመዘምራኑ መሪ ከናንያና የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሌዋውያን ከጥሩ በፍታ የተሠራ ልብስ ለብሰው ነበር።

28 በዚህ ዐይነት መላው እስራኤላውያን ጥሩምባና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽል እያንሿሹ፥ መሰንቆና በገና እየደረደሩ በሆታና በእልልታ የቃል ኪዳኑን ታቦት አጅበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

29 ታቦቱ ወደ ከተማይቱ በመግባት ላይ ሳለ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ንጉሥ ዳዊት በደስታ ሲያሸበሽብና ሲዘል በመስኮት ተመለከተች፤ በልብዋም ናቀችው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告