1 ዜና መዋዕል 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት በኢየሩሳሌም ያከናወናቸው ሥራዎች ( 2ሳሙ. 5፥11-16 ) 1 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፤ ከእነርሱም ጋር ለዳዊት ቤተ መንግሥት የሚሠሩለት የሊባኖስ ዛፍ ግንድ የያዙ አናጢዎችና ግንበኞች ነበሩ፤ 2 ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን እንዳበለጸገለት ተገነዘበ። 3 በዚያም በኢየሩሳሌም ዳዊት ብዙ ሚስቶችን አገባ፤ ብዙ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ 4 በኢየሩሳሌም ሳለ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሻሙዓ፥ ሾባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ 5 ይብሐር፥ ኤሊሹዓ፥ ኤሊጴሌት፥ 6 ኖጋህ፥ ኔፌግ፥ ያፊዓ፥ 7 ኤሊሻማዕ፥ ቤኤልያዳና ኤሊፌሌት ተብለው የሚጠሩት ናቸው። ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ላይ የተቀዳጀው ድል ( 2ሳሙ. 5፥17-25 ) 8 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ እርሱን ለመማረክ ሠራዊታቸውን አዘመቱ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ከእነርሱ ጋር ጦርነት ለመግጠም ወጣ፤ 9 ፍልስጥኤማውያን ወደ ራፋይም ሸለቆ መጥተው ወረሩአት፤ 10 ዳዊትም “በፍልስጥኤማውያን ላይ ጦርነት ልክፈትን? በእነርሱስ ላይ ድልን ታጐናጽፈኛለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ፥ አደጋ ጣልባቸው! እኔም ድልን አጐናጽፍሃለሁ!” አለው። 11 ስለዚህ ዳዊት ባዓልፈራጺም ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጥሎ ድል ካደረጋቸው በኋላ “የጠላትን ሠራዊት እንደ ጐርፍ ጥሼ እንዳልፍ እግዚአብሔር ረዳኝ” አለ፤ ከዚያም በኋላ ያ ስፍራ “ባዓልፈራጺም” ተብሎ ተጠራ፤ 12 ፍልስጥኤማውያን ሲሸሹ ጣዖቶቻቸውን ጥለው ሄዱ፤ ዳዊትም ጣዖቶቹ በሙሉ እንዲቃጠሉ ትእዛዝ ሰጠ። 13 ፍልስጥኤማውያን ደግሞ ወደ ሸለቆው ተመልሰው እንደገና መውረር ጀመሩ፤ 14 ዳዊትም እንደገና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም “ከኋላ በኩል ዞረህ በሾላ ዛፎች አጠገብ በመሆን አደጋ ጣልባቸው እንጂ በዚህ በኩል ሽቅብ ወጥተህ በመሰለፍ አደጋ አትጣልባቸው፤ 15 እኔ ፊት ፊትህ ሄጄ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ድል ስለምመታ በዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ አደጋ ጣል” አለው። 16 ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማድረግ ፍልስጥኤማውያንን ከገባዖን እስከ ጌዜር ድል አድርጎ አባረራቸው 17 የዳዊትም ዝና በየቦታው ተሠራጨ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተፈራ እንዲሆን አደረገ። |