1 ዜና መዋዕል 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየቃል ኪዳኑን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ መሞከሩ ( 2ሳሙ. 6፥1-11 ) 1 ንጉሥ ዳዊት የሻለቅነትና የመቶ አለቅነት ማዕርግ ካላቸው የጦር አለቆች ጋር ተመካከረ፤ 2 ከዚያም በኋላ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲል አስታወቀ፥ “እናንተ ከተስማማችሁበትና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፥ የቀሩት የአገራችን ሰዎች፥ ካህናትና ሌዋውያን ወደሚኖሩባቸው ታናናሽ ከተማዎች መልእክተኞች ልከን ወደዚህ መጥተው ከእኛ ጋር እንዲሰበሰቡ እንንገራቸው፤ 3 በሳኦል ዘመነ መንግሥት ችላ ብለነው የነበረውንም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ሄደን እናመጣለን።” 4 ሕዝቡም በሐሳቡ ደስ በመሰኘት ተስማሙ። 5 ስለዚህም ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደቡብ በኩል እስከ ግብጽ ግዛት ድንበር፥ በሰሜን እስከ ሐማት መተላለፊያ ድረስ በመላው እስራኤል የሚገኘውን ሕዝብ በአንድነት ሰበሰበ። 6 ዳዊትና ሕዝቡ ሁሉ በኪሩቤል ክንፎች ላይ የተቀመጠውን፥ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ያመጡ ዘንድ በይሁዳ ግዛት ባዓላ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ቂርያትይዓሪም ከተማ ሄዱ፤ 7 የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤ ዑዛና አሕዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር፤ 8 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ መሰንቆና በገና እየደረደሩ፥ አታሞ እየመቱ፥ ጸናጽል እያንሿሹና እምቢልታ እየነፉ በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ለእግዚአብሔር ክብር ያሸበሽቡ ነበር። 9 ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ ሠረገላውን የሚጐትቱት በሬዎች ሲፋንኑ አደናቀፋቸው፤ ዑዛም እጆቹን ዘርግቶ የቃል ኪዳኑን ታቦት በመደገፍ ያዘ፤ 10 ዑዛ ታቦቱን በመንካቱ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ወዲያውኑ በሞት ቀሠፈው፤ ስለዚህም ዑዛ በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ፤ 11 ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ “ፔሬጽ ዑዛ” ተብሎ ይጠራል፤ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ዑዛን ስለ ገደለው ዳዊት እጅግ ተበሳጨ። 12 ከዚህ በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈራ “እንግዲህ ይህን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቴ እንዴት መውሰድ እችላለሁ?” አለ፤ 13 ስለዚህም ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድ ፈንታ የጋት ከተማ ነዋሪ በሆነው፥ ዖቤድኤዶም ተብሎ በሚጠራው ሰው ቤት ተወው። 14 ታቦቱም በዚያ ሦስት ወር ቈየ፤ እግዚአብሔርም የዖቤድኤዶምን ቤተሰብና የእርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባረከ። |