1 ዜና መዋዕል 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከብንያም ነገድ ቀደም ብለው ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች 1 ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በጺቅላግ በነበረ ጊዜ ከእርሱ ጋር የተቀላቀሉት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም መካከል የጦር ጀግኖች ነበሩባቸው። 2 እነርሱም ከብንያም ነገድ ስለ ነበሩ የሳኦል ዘመዶች ነበሩ፤ እነርሱ በቀኝና በግራ እጃቸው ፍላጻ የመወርወርና ድንጋይ የመወንጨፍ ችሎታ ያላቸው ነበሩ፤ 3-7 እነርሱ የጊብዓ ተወላጅ የሆነው የኢሸማዓ ልጆች በሆኑት በአሒዔዜርና በዮአሽ አመራር ሥር ነበሩ። የወታደሮቹም ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦ የዓዝማዌት ልጆች ይዚኤልና ፔሌጥ፥ የዐናቶት ተወላጆች የሆኑት በራካና ኢዩ፥ ዝነኛ ወታደር የነበረው፥ በኋላም የሠላሳዎቹ ኀያላን መሪዎች ከሆኑት አንዱ የሆነው፥ የገባዖን ተወላጅ ዩሽማዕያ፥ የገዴራ ተወላጆች የሆኑት ይርመያ፥ ያሕዚኤል፥ ዮሐናንና ዮዛባድ፥ የሐሪፍ ተወላጆች የሆኑት ኤልዑዛይ፥ ያሪሞት፥ በዓልያ፥ ሸማርያና ሸፋጥያ፥ ከቆሬ ጐሣዎች የሆኑት ኤልቃና፥ ዩሺያሁ፥ ዐዛርኤል፥ ዮዔዜርና ያሸብዓም፥ የገዶር ተወላጆች የሆኑት የይሮሐም ልጆች ዮዔላና ዘባድያ። ከጋድ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች 8 ዳዊት በበረሓ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ሳለ ከጋድ ነገድ መጥተው ከእርሱ ሠራዊት ጋር የተባበሩት ዝነኞችና የጦር ልምድ ያላቸው ወታደሮች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፤ እነርሱ ጋሻና ጦር ይዘው በመዋጋት የታወቁ ነበሩ፤ አስፈሪነታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ፈጣንነታቸው በተራራ ላይ እንደሚዘል ሚዳቋ ነበር፤ 9-13 የእነርሱም ስም በሚከተለው ሁኔታ በየማዕርጋቸው በቅደም ተከተል ተራ ተዘርዝሮአል፦ ዔዜር፥ አብድዩ ኤሊአብ፥ ሚሽማና፥ ኤርምያስ፥ ዓታይ፥ ኤሊኤል፥ ዮሐናን፥ ኤልዛባድ፥ ኤርምያስ ማክባናይ። 14 ከጋድ ነገድ ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ የሺህ አለቅነት ማዕርግ ያላቸው የበላይ መኰንኖችና የመቶ አለቅነት ማዕርግ ያላቸው የበታች መኰንኖች ነበሩ። 15 እነዚህም የጋድ ነገድ አባሎች በአንድ ወቅት የዓመቱ የመጀመሪያ ወር እንደ ገባ፥ የዮርዳኖስም ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ ሳለ ወንዙን ተሻገሩ፤ ከወንዙ በሰተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ በሸለቆዎቹ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አባረሩ። ከብንያምና ከይሁዳ ነገዶች ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች 16 አንድ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች የተውጣጡ ጥቂት ሰዎች ዳዊት ወዳለበት ምሽግ ሄዱ፤ 17 ዳዊትም ወደ እነርሱ ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ወደዚህ የመጣችሁት በወዳጅነት ልትረዱኝ ከሆነ መልካም ነው፤ በደስታ እቀበላችኋለሁ፤ ከእኛም ጋር ሁኑ! እኔ ምንም ሳላደርጋችሁ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ ግን የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ ተመልክቶ ይፍረደው።” 18 የእግዚአብሔር መንፈስ የሠላሳዎቹ መሪ በሆነው በዐማሳይ ላይ ወረደ፤ እርሱም፦ “ዳዊት ሆይ! እኛ የአንተ ነን! የእሴይ ልጅ ዳዊት ሆይ! እኛ ከአንተ ጋር ነን! ለአንተና አንተን ለሚረዱ ሁሉ ሰላም ይሁን! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በመሆን ይረዳሃል፤” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ ዳዊትም እነርሱን በደስታ ተቀብሎ በሠራዊቱ ውስጥ አለቆች አደረጋቸው። ከምናሴ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች 19 ዳዊት፥ ንጉሥ ሳኦልን ለመውጋት ከፍልስጥኤማውያን ጋር በዘመተ ጊዜ ከምናሴ ነገድ የሆኑ ጥቂት ወታደሮች ከዳዊት ጋር ለመተባበር ሄዱ፤ ሆኖም የፍልስጥኤማውያን መሪዎች “ዳዊት እኛን ከድቶ ወደ ቀድሞ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ብለው ስለ ፈሩ ከተመካከሩ በኋላ ወደ ቲግላግ እንዲመለስ አደረጉት፤ 20 ከምናሴ ነገድ ዳዊት በተመለሰ ጊዜ ወደ እርሱ የሄዱት ወታደሮች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦ ዓድናሕ፥ ዮዛባድ፥ ይዲዕኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባድ፥ ኤሊሁና ጺለታይ፤ እነዚህ ሁሉ በምናሴ ግዛት ሳሉ የሺህ አለቅነት ማዕርግ የነበራቸው ናቸው። 21 ሁሉም ዝነኞች ወታደሮች ነበሩ። የጠላት ወታደሮች በሚያጠቁበት ጊዜ ዳዊትን ይረዱ ነበር፤ በሠራዊቱም ውስጥ የጦር አለቆች ሆነዋል። 22 በየቀኑ አዳዲስ ሰዎች ወደ ዳዊት ሠራዊት እየመጡ ይቀላቀሉ ስለ ነበር ብዙ ሳይቈይ የዳዊት ሠራዊት እጅግ የበዛና ኀያል ሆነ። የዳዊት ሠራዊት ብዛት 23-37 ዳዊት በኬብሮን ሳለ ብዙ የሠለጠኑ ወታደሮች ወደ እርሱ ሠራዊት ገቡ፤ እግዚአብሔር በሰጠውም የተስፋ ቃል መሠረት በሳኦል እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ብዙ ርዳታ አደረጉለት፤ ቊጥራቸውም እንደሚከተለው ነበር፦ ከይሁዳ ነገድ፦ ጋሻና ጦር በሚገባ የታጠቁ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ወታደሮች፥ ከስምዖን ነገድ፦ በሚገባ የሠለጠኑ ሰባት ሺህ አንድ መቶ ወታደሮች፥ ከሌዊ ነገድ፦ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች፤ የአሮን ዘሮች የሆኑት የዮዳሄ ተከታዮች ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ታዋቂ ጦረኛ ከሆነው ከጻዶቅ ዘመዶች፦ ኻያ ሁለት የጦር አዛዦች፥ የሳኦል ወገን ከሆነው ከብንያም ነገድ፦ ሦስት ሺህ ሰዎች፤ ይሁን እንጂ ከብንያም ነገድ አብዛኛው ሕዝብ ለሳኦል ያላቸውን ታማኝነት እንደ ቀጠሉ ነበሩ። ከኤፍሬም ነገድ፦ ኻያ ሺህ ስምንት መቶ ሰዎች ሲሆኑ፥ ሁሉም በየጐሣቸው ዝነኞች የሆኑ ጀግኖች ነበሩ። በምዕራብ በኩል ካለው ከምናሴ ነገድ፦ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ሲሆኑ፥ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በተለይ የተመረጡ ናቸው። ከይሳኮር ነገድ፦ ሁለት መቶ መሪዎች ሲሆኑ፥ በእነርሱ አመራር ሥር ያሉትንም ያጠቃልላል፤ እነዚህ መሪዎች እስራኤል ምን ማድረግና መቼ ማድረግ እንደሚገባት የሚያውቁ ናቸው። ከዛብሎን ነገድ፦ እምነት የሚጣልባቸው ለጦርነት ዝግጁዎች የሆኑ በማንኛውም መሣሪያ መጠቀም የሚችሉ ኀምሳ ሺህ ወታደሮች፤ ከንፍታሌም ነገድ፦ አንድ ሺህ የጦር መሪዎችና ጋሻና ጦር ያነገቡ ሠላሳ ሰባት ሺህ ወታደሮች ነበሩ። ከዳን ነገድ፦ ኻያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ የሠለጠኑ ወታደሮች ነበሩ። ከአሴር ነገድ፦ አርባ ሺህ ለጦርነት የተዘጋጁ ወታደሮች ነበሩ። ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ካሉት ከሮቤል፥ ከጋድና ከምናሴ ነገዶች፦ በማንኛውም ዐይነት መሣሪያ የመጠቀም ችሎታ ያላቸው አንድ መቶ ኻያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ። 38 እነዚህ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ወታደሮች ዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ ለማንገሥ ቊርጥ ውሳኔ አድርገው ወደ ኬብሮን ሄዱ፤ የቀሩትም እስራኤላውያን በዚሁ ዓላማ በአንድነት ተስማምተው ነበር፤ 39 እነዚህ ሁሉ የገዛ ወገኖቻቸው ያዘጋጁላቸውን በደስታ እየተመገቡና እየጠጡ፥ ሦስት ቀን ከዳዊት ጋር ቈዩ፤ 40 በስተ ሰሜን በኩል ካሉት ከይሳኮር፥ ከዛብሎንና ከንፍታሌም ነገዶች ሳይቀር ብዙ ሰዎች በአህያ፥ በግመል፥ በበቅሎና በበሬ ብዙ ምግብ፥ ዱቄት፥ በለስ፥ ዘቢብ፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት በመጫን ይዘው መጥተው ነበር፤ እንዲሁም ዐርደው የሚበሉአቸውን ብዙ የቀንድ ከብቶችና በጎችን ይዘው መጥተዋል፤ ይህም ሁሉ በመላው አገሪቱ ላይ የሚገኘው ሕዝብ የተሰማውን ደስታ የሚገልጥ ነበር። |