1 ዜና መዋዕል 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ሆነ ( 2ሳሙ. 5፥1-10 ) 1 እስራኤላውያን ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት ሄደው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ሁላችን የሥጋ ዘመዶችህ ነን፤ 2 ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንኳ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ጦርነት የምትመራ አንተ ነበርክ፤ ‘ሕዝቤን እስራኤልን የምትመራና የምታስተዳድር አንተ ነህ’ ብሎ አምላክህ እግዚአብሔር ነግሮሃል።” 3 በዚያም ዐይነት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ንጉሥ ዳዊት መጡ፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር የተቀደሰ ስምምነት አደረገ፤ እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡ ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት። ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል ማድረጉ 4 ንጉሥ ዳዊትና መላው የእስራኤል ሕዝብ ሄደው በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ አደጋ ጣሉ፤ በዚያን ጊዜ የከተማይቱ ስም “ኢያቡስ” ይባል ነበር፤ በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ኢያቡሳውያን ናቸው። 5 ኢያቡሳውያን ዳዊትን “ከቶ ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን በጽዮን የሠሩትን ምሽጋቸውን ያዘ፤ ከዚያም በኋላ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ትጠራ ጀመር። 6 ዳዊትም “በመጀመሪያ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ የሚጥል ሰው የሠራዊቱ አዛዥ ይሆናል!” አለ፤ የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ሄዶ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ በመጣሉ የሠራዊቱ አዛዥ ሆነ፤ 7 ዳዊትም ሄዶ በምሽጉ ውስጥ ስለ ኖረ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ተጠራች። 8 ዳዊት ከኰረብታው በስተ ምሥራቅ በኩል በዐፈር ከተደለደለው ስፍራ አንሥቶ ከተማይቱን እንደገና ሠራ፤ ኢዮአብም በበኩሉ የቀረውን የከተማይቱን ክፍል ሠራ፤ 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመሆኑ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ። ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ( 2ሳሙ. 23፥8-39 ) 10 ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ስም ዝርዝር ከዚህ በታች እንደሚከተለው ነው፦ እነርሱም ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነው እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ዳዊት እንዲነግሥ በጣም ረድተዋል። መንግሥቱም ጽኑና ኀያል እንዲሆን አድርገዋል። 11 የመጀመሪያው የሐክሞን ጐሣ ወገን የሆነው ያሾብዓም ሲሆን፥ እርሱም የሦስቱ ኀያላን መሪ ነበር፤ እርሱ በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን አንሥቶ በአንድ ፍልሚያ ብቻ ሁሉንም ገደላቸው፤ 12 ከእርሱ የሚቀጥል ከሦስቱ ኀያላን አንዱ የሆነው ሌላው ከአሖሕ ጐሣ የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነው፤ 13 እርሱ ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በተሰለፉ ጊዜ በፓስደሚም ከዳዊት ጋር ነበር፤ የገብስ ማሳ በነበረበት ቦታ እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14 እርሱና ተከታዮቹ በዚያው በማሳው ውስጥ ፍልስጥኤማውያንን ተቋቊመው ወጉአቸው፤ እግዚአብሔርም ታላቅ ድልን አጐናጸፋቸው። 15 አንድ ቀን ከሠላሳዎቹ ጀግኖች ሦስቱ ወታደሮች ፍልስጥኤማውያን በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ፥ ዳዊት በሚኖርበት በአዱላም ዋሻ አጠገብ ወዳለው አለት ሄዱ፤ 16 ዳዊት በዚያን ጊዜ፥ በተመሸገ ኰረብታ ላይ ነበር፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት አንዱ ቡድን ቤተልሔምን በመውረር ያዘ። 17 ዳዊትም “በቤተልሔም ቅጽር በር አጠገብ ካለው የውሃ ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን በሰጠኝ!” ብሎ ተመኘ። 18 በዚህን ጊዜ ሦስቱ ዝነኛ ወታደሮች የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር ጥሰው በማለፍ ከጒድጓዱ ውሃ ቀዱና ለዳዊት ይዘውለት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጠጣው አልወደደም፤ በዚህ ፈንታ ለእግዚአብሔር እንደ መባ አድርጎ አፈሰሰው። 19 “እኔ ይህን ውሃ መጠጣት ከቶ አልችልም! እኔ ይህን ውሃ ብጠጣ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚያን ኀያላን ሰዎች ደም እንደ ጠጣሁ ይቈጠራል!” አለ። ስለዚህም ውሃውን ይጠጣ ዘንድ አልወደደም፤ እንግዲህ ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፈጸሙአቸው የጀግንነት ተግባሮች እነዚህ ናቸው። 20 የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ዝነኞች ወታደሮች የበላይ አለቃ ነበር፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎችን ገድሎ ስለ ነበር እንደ ሦስቱ ዝነኞች ወታደሮች ታዋቂ ሆነ፤ 21 ከሦስቱ ጀግኖች መካከል እንደ አንዱ ባይቈጠርም በሠራው ጀብዱ ከእነርሱ ይበልጥ እጥፍ ድርብ ክብር በማግኘቱ የእነርሱ አለቃ ለመሆን በቃ። 22 በቃብጽኤል ምድር የዮዳሄ ልጅ በናያ ዝነኛ ወታደር ነበር፤ እርሱ ሁለት የታወቁ ሞአባውያን ጦረኞችን ከመግደሉም ሌላ ብዙ የጀግንነት ሥራ ፈጽሞአል፤ አንድ ጊዜ በምድር ላይ ዐመዳይ በወረደበት ቀን ወደ አንድ ዋሻ ወርዶ አንበሳ ገደለ፤ 23 እንዲሁም በጣም ትልቅ ጦር ይዞ የነበረውን፥ ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ የሆነውን፥ አንድ ግዙፍ ግብጻዊ ገድሎአል፤ ይኸውም በናያ በእጁ ከበትር በስተቀር ሌላ የጦር መሣሪያ ሳይዝ ወደ ግብጻዊው ቀርቦ ከመታው በኋላ ግብጻዊው ይዞት የነበረውን የሸማኔ መጠቅለያ የሚመስለውን የገዛ ጦሩን ቀምቶ ገደለው። 24 እንግዲህ ከሠላሳዎቹ አንዱ የሆነው በናያ የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች እነዚህ ናቸው፤ 25 ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ታዋቂ ቢሆንም በዝነኛነቱ ከሦስቱ ኀያላን ጀግኖች ደረጃ አልደረሰም፤ ዳዊትም በናያን የክብር ዘብ አዛዥ በማድረግ ሾሞት ነበር። 26-47 ከሠላሳዎቹ መካከል የሌሎቹ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል፥ የቤተልሔሙ ተወላጅ የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፥ የሐሮድ ተወላጅ ሻሞት፥ የፌሌጥ ተወላጅ የሆነው ሔሌጽ፥ የተቆዓ ተወላጅ የሆነው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፥ የዐናቶት ተወላጅ የሆነው አቢዔዜር፥ የሑሻ ተወላጅ የሆነው ሲበካይ፥ የአሖሕ ተወላጅ የሆነው ዒላይ፥ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማህራይ፥ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው የባዕና ልጅ ሔሌድ፥ በብንያም ግዛት የምትገኘው የጊብዓ ተወላጅ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው በናያ፥ በጋዓሽ አጠገብ ባሉት ሸለቆዎች የተወለደው ሑራይ፥ የዓረባ ተወላጅ የሆነው አቢኤል፥ የባሕሩም ተወላጅ የሆነው ዓዝማዌት፥ የሻዓልቦን ተወላጅ የሆነው ኤልያሕባ፥ የጊዞን ተወላጅ የሆነው ሃሼም፥ የሃራር ተወላጅ የሆነው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ የሀራር ተወላጁ የሳካር ልጅ አሒአም፥ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ የመኬራ ተወላጅ የሆነው ሔፌር፥ የፐሎን ተወላጅ የሆነው አሒያ፥ የቀርሜሎስ ተወላጅ የሆነው ሔጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ናዕራይ፥ የናታን ወንድም ዮኤል፥ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥ የዐሞን ተወላጅ የሆነው ጼሌቅ፥ የበኤሮት ተወላጅና የኢዮአብ ጋሻጃግሬ የነበረው ናሕራይ፥ የያቲር ተወላጆች የሆኑት ዒራና ጋሬብ፥ ሒታዊው ኦርዮን፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ የሺዛ ልጅ ዐዲና፤ (ይህ ሰው የራሱ ቡድን የሆኑ ሠላሳ ወታደሮችን እንደ ያዘ ከሮቤል ነገድ የታወቀ ነበር፤) የማዕካ ልጅ ሐናን፥ የሚታን ተወላጅ የሆነው ኢዮሣፍጥ፥ የዐሽተራ ተወላጅ የሆነው ዑዚያ፥ የዓሮዔር ተወላጅ የሆነው የሆታም ልጆች ሻማዕና ይዒኤል፥ የቲጺ ተወላጅ የሆነው የሺምሪ ልጆች ይዲዕኤልና ዮሐ፥ የማሐዋ ተወላጅ የሆነው ኤሊኤል፥ የኤልናዓም ልጆች ይሪባይና ዮሻውያ፥ የሞአብ ተወላጅ የሆነው ዩትማ፥ የጾባ ተወላጆች የሆኑት ኤሊኤል፥ ዖቤድና ያዕሲኤል። |