Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የንጉሥ ሳኦል መሞት
( 1ሳሙ. 31፥1-13 )

1 ፍልስጥኤማውያን መጥተው በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጣሉ፤ እስራኤላውያንም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ በዚያም ጦርነት በጊልቦዓ ተራራ ላይ ብዙ እስራኤላውያን ተገደሉ፤

2 ፍልስጥኤማውያን ግን ሳኦልንና ልጆቹን ተከታትለው ከሳኦል ልጆች ሦስቱን ዮናታንን፥ አቢናዳብንና ማልኪሹዓን ገደሉ፤

3 ሳኦል በነበረበት ግንባር ጦርነቱ እጅግ ተፋፍሞ ስለ ነበር ሳኦል በጠላት ፍላጻ ተመትቶ ክፉኛ ቈሰለ፤

4 እርሱም በዚህ ጊዜ ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ አረማውያን መሳለቂያ እንዳያደርጉኝ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው፤ ወጣቱ ግን ይህን ለማድረግ እጅግ ስለ ፈራ አላደረገውም፤ ስለዚህም ሳኦል የራሱን ሰይፍ መዞ በመሬት ላይ በመትከል በላዩ ላይ ወደቀ፤

5 ወጣቱም የሳኦልን መሞት ባየ ጊዜ እርሱም የገዛ ሰይፉን በመሬት ላይ በመትከል በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ።

6 ስለዚህ ሳኦልና ሦስት ወንዶች ልጆቹ በአንድ ላይ ሞቱ፤ የመንግሥቱም ፍጻሜ ሆነ።

7 በኢይዝራኤል በሸለቆው ይኖሩ የነበሩት እስራኤላውያን ሠራዊቱ እንደ ሸሸ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ በሰሙ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቻቸውን ያዙ።

8 በጦርነቱ ማግስት ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን እስራኤላውያን ለመግፈፍ በሄዱ ጊዜ የሳኦልና የልጆቹ ሬሳ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተጋድሞ አገኙ፤

9 የሳኦልን ራስ ቈርጠው የጦር መሣሪያውን ከገፈፉ በኋላ በመልእክተኞች አስይዘው የምሥራቹን ለአማልክታቸውና ለሕዝባቸው ይነግሩላቸው ዘንድ ላኩአቸው።

10 የሳኦልን የጦር መሣሪያዎች በአማልክታቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም ዳጎን ተብሎ በሚጠራው አምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሰቀሉት።

11 በገለዓድ የሚገኘው የያቤሽ ሕዝብ፥ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ የፈጸሙትን ግፍ በሰሙ ጊዜ፥

12 ኀያላን የሆኑ ሰዎች ሄደው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ በመውሰድ ወደ ያቤሽ አመጡ፤ በዚያም በወርካ ዛፍ ሥር ከቀበሩአቸው በኋላ ሰባት ቀን በሙሉ ጾሙ።

13-14 ሳኦል ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ ምክንያት ሞተ፤ እርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈጸመም፤ እንዲያውም የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን በመጠየቅ መመሪያ ለማግኘት ሞከረ እንጂ እግዚአብሔርን አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አስተላለፈ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告