本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ጥበብ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጥበብና ታሪክ ከአዳም እስከ ሙሴ 1 የመጀመሪያውን ሰው፥ የዓለምን አባት፥ በመልካም ሁኔታ ይቀረጽ ዘንድ፥ ከወደቀበት ያዳነችው እርሷ ናት፤ 2 ሁሉን ይገዛም ዘንድ ኃየልን ሰጠችው። 3 ክፉው ሰው በተቆጣ ጊዜ ግን እርሷን ተዋት፤ በንዴት ወንደሙን በመግደሉ በጥፋት ላይ ወደቀ። 4 በእርሱ ጥፋት መሬት በውሃ በተጥለቀለቀች ጊዜ፥ አሁንም ያዳነችው ጥበብ ናት። ጻድቁን ሰው በእንጨት አንሳፋ አዳነችው። 5 ሰዎች ክፉ በመፈጸም ሲያድሙ፥ እንዲበጣበጡ ተፈረደባቸው፤ ያንጊዜ ጻድቁን ሰው ለየች፤ በእግዚአብሔርም ፊት አቀረበች፤ ከልጁም ኀዘን አበረታችው። 6 ክፉዎች በጠፉ ጊዜ ጻድቁን ያዳነች እርሷ ናት፤ ስለ ክፋታቸው ምስክር ይሆን ዘንድ፥ ከነደደው መሬት፥ 7 ተክሎች የማይበስል ፍሬ ከተሸከሙበት፥ ላላመነች ነፍስ የቆመው መታሰቢያ የጨው ዓምድ ሆኖ ከቀረበት፥ በአምስቱ ከተሞች ላይ ከወረደው እሳት ሸሽቶ እንዲያመልጥ ረድታዋለች። 8 የጥበብን መንገድ ባለመሻት፥ ጥሩውን ለማወቅ ካለመቻላቸው በላይ የስሕተታቸውን መታሰቢያ ጥለው አልፈዋል፤ በዚህም ገበናቸውን ሁሉም ያየዋል። 9 ጥበብ ግን አገልጋዮቿን ሁሉ፥ ከመከራ ታደገቻቸው። 10 ከወንድሙ ቁጣ የሚሸሸውን ጻድቅ ሰው፥ በቀና መንገዶች መራችው፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት አሳየችው፤ ስለ ቅዱስ ነገሮችም ያውቅ ዘንድ አስተማረችው፤ ድካሙ ፍሬ እንዲያፈራ አደረገች፤ የጥረቱንም ዋጋ ሰጠችው። 11 ከጨቋኞችና ከስግብግቦች ጋር ስፋለም፥ ከጐኑ ቆመች፤ ባለጸጋም አደረገችው። 12 ከጠላቶቹ ጠበቀችው፤ ካጠመዱበትም ወጥመድ አወጣችው። በመራራዉ የትግል ወቅት ሸለመችው። የተቀደሰ ተግባር ከሁሉም በላይ መሆኑን አስተማረችው። 13 በተሸጠ ጊዜ ከጻድቁ ሰው አልራቀችም፤ ከኃጢአትም መንጥቃ አወጣችው። 14 ከጉድጓድ ውስጥ አብራው ገባች፤ በሰንሰለት በታሰረ ጊዜ አልተወችውም፤ በትረ መንግሥቱን እስኪጨብጥ፥ በጨቋኞችም ላይ ሥልጣንን እስኪያገኝ፥ ከጐኑ አልጠፋችም። በውሸት ያሙትን ሁሉ፥ ሐሰተኞች እንደ ሆኑ አግልጣለች፤ ዘላለማዊ ክብርንም አጐናጽፋዋለች። ወደ ተስፋይቱ ሀገር መመለስ 15 ንጹሕ ዘር የሆነውን የቀደሰ ሕዝብ፥ ከጨቋኞች መዳፍ የታደገችው ጥበብ ነች። 16 በጌታ አገልጋይ ነፍስ ውስጥ ዘልቃ፥ በታምራትና በምልክቶች አስፈሪ ነገሥታትን የተቋቋመች ጥበብ ናት። 17 ለተቀደሱ ሰዎች የልፋታቸውን ዋጋ ከፍላለች፤ በአስደናቂ መንገድም መራቻቸው፤ በቀን ተገን፤ በሌሊት የኮከብ ብርሃን ሆነችላቸው። 18 ቀይ ባሕርን አሻገረቻቸው፤ በግዙፍ የውሃ አካልም ውስጥ መራቻቸው፤ 19 ጠላቶቻቸውን ግን አስመጠች፤ ኋላም ከጥልቁ ጉድጓድ ተፋቻቸው። 20 ስለዚህ ጻድቃን ክፉዎቹን በረበሯቸው፤ ጌታ ሆይ የተቀደሰውን ስምህንም አመስግኑ፤ በአንድነት ጠባቂ ክንድህን አወድሱ፤ 21 ጥበብ የዱዳዎችን አንደበት ከፍታለች፤ የሕፃናትንም ምላስ ፈትታለችና። |