本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ጦቢት 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መቃብሩ 1 ከበሉና ከጠጡ በኋላ ወደ መኝታ ቤታቸው ለመሄድ ተነሡ፤ ወጣቱንም ወሰዱትና ወደ ተዘጋጀው መኝታ ቤት አስገቡት። 2 ጦብያ ሩፋኤል የነገረውን አስታወሰ፤ ከከረጢቱ የዓሣውን ጉበትና ልብ አውጥቶ በዕጣን ማጨሻው ላይ አደረገው። 3 የዓሣው ሽታ ጋኔኑን አሸሸው፤ ጋኔኑ በአየር ላይ ወደ ግብጽ አገር ሸሸ፤ ሩፋኤል ወዲያውኑ ተከታትሎ ያዘውና እጅና አግሩን አሰረው። 4 የሣራ ወላጆች ወጡና በሩን ከኋላቸው ዘጉት፤ በዚያን ጊዜ ጦብያ ከአልጋው ተነሣና ሣራን “እኀቴ ተነሽ ጌታችን ጸጋውንና ጥበቃውን እንዲያበዛልብ መጸለይና መለመን አለብን” አላት። 5 እርሷም ተነሣች፤ እንዲጠብቃቸው መጸለይና መለመን ጀመሩ፥ እንዲህም ሲል መጸለይ ጀመረ “የአባቶቻችን አምላክ ሆይ ብሩክ ነህ፤ ስምህም ለዘለዓለም ዓለም የተባረከ ነው፤ ሰማያትና የፈጠርካቸው ሁሉ ለዘለዓለም ይባርኩህ፤ 6 አዳምን የፈጠርህ አንተ ነህ፥ ረዳትና አጋዥ እንድትሆነው ሚስቱን ሔዋንን የፈጠርህለት አንተ ነህ፤ የሰው ዘር ሁሉ የተወለደው ከሁለቱ ነው። ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም፥ እሱን የምትመስል ረዳት እንፈጠርለት’ ያልህ አንተ ነህ። 7 አሁንም ይህችን እኀቴን የማገባት በዝሙት መንፈስ ተይዤ ሣይሆን በእውነተኛነት ነው፤ በእኔም በእርሷም ላይ ምሕረትህን አውርድልን፤ አብረንም ለሽምግልና አብቃን። 8 ሁለቱም አብረው ‘አሜን አሜን’ አሉ። 9 ከዚህ በኋላ አብረው አደሩ። ራጉኤል ግን ተነሣና አገልጋዮቹን ጠራ፤ ከእርሱ ጋር ሄዱና የመቃብር ቦታ ቆፈሩ፤ 10 ‘እሱም ይሞታል እኛም የሰዎች መሳቂያና ማላገጫ እንሆናለን’ ብሎ አስቧልና።” 11 መቃብሩን ቆፍረው ከጨረሱ በኋላ ራጉኤል ወደ ቤቱ ሄዳና ሚስቱን ጠራት፤ 12 እንዲህም አላት፦ “ጦብያ በሕይወት እንዳለ ለማየት ከአገልጋዮቹ አንዲቱን ወደ መኝታ ቤቱ ላኪ፤ ሞቶ ከሆነ ማንም ሰው ሳያውቅ እንድንቀብረው።” 13 ከዚያም አገልጋይቱን ላኳት፥ እስዋም ፋኖሱን አብርታ በሩን ከፍታ ወደ ውስጥ ገባች፥ ሁለቱም ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዷቸው አገኘቻቸው፤ 14 ወጣችና “እሱ አልሞተም ሁሉም ነገር ሰላም ነው።” አለቻቸው። 15 ከዚህ በኋላ ራጉኤል የሰማዩን አምለክ በእነዚህ ቃላት እንዲህ ሲል ባረከ “አምላኬ ሆይ ንጹሕ በሆነ በረከት አንተ ብሩክ ነህ፤ ለዘለዓለሙ ብሩክ ሁን። 16 ደስ ስላሰኘኸኝ አንተ ብሩክ ነህ፤ ወሰን የሌለውን ምሕረትህን አሳየኸን እንጂ የፈራሁት አልደረሰም። 17 ለወላጆቻቸው አንድ የሆኑትን ልጆች ስለራራህላቸው አንተ ብሩክ ነህ። አሁንም ጌታ ሆይ ምሕረትህንና ጥበቃህን ስጣቸው፤ ሕይወታቸውን በደስታና በምሕረት እንዲመሩ አድርጋቸው።” 18 ከዚህ በኋላ አገልጋዮቹን ሳይነጋ መቃብሩን እንዲደፍኑት አዘዛቸው። 19 ሚስቱ ዳቦ በብዛት እንድትጋግር ነገራት፤ ወደ ከብቶቹ መንጋ ሄደና ሁለት ሰንጋዎችና አራት ሙክቶች አምጥቶ ታርደው እንዲዘጋጁ አዘዘ፥ ዝግጅቱም ተጀመረ። 20 እስሱም ጦብያን ጠርቶ “እንግዲህ ወዴትም ሳትሄዱ እዚህ እየበላህና እየጠጣህ ዐሥራ አራት ቀን ከእኔ ጋር ትቆያለህ፥ ብዙ መከራ የደረሰባትን ልጄንም ታስደስታታለህ። 21 ከዛ በኋላ የንብረቴን ግማሹን ውሰድና ያለ ምንም ችግር ይዘሃት ወደ አባትህ ቤት ሂድ፤ የቀረውን ግማሽ ደግሞ እኔና ሚስቴ ስንሞት የእናንተ ይሆናል፤ በርታ ልጄ፥ እኔ አባትህ ነኝ፥ ኤድናም እናትህ ናት፥ ከእኀትህ ወላጆች እንደ ሆንን የአንተም ነን፥ በርታ ልጄ።” |