本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ሲራክ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በፈተና ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት 1 ልጄ ሆይ ጌታን ማገልገል ስትፈልግ፤ እራስህን ለፈተና አዘጋጅ፤ 2 ቅን ልብ ይኑርህ፥ ቆራጥ ሁን፥ በጭንቀት ጊዜ አትታወክ፥ 3 ወደ እግዚአብሔር ተጠጋ፥ ከሱ አትራቅ፥ በመጨረሻ ቀኖችህም ክብርን ትጐናጸፋለህ። 4 የሚመጣብህን ነገር ሁሉ ተቀበለው፤ በመከራ ጊዜ ግራ ብትጋባም ታገስ። 5 ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ፥ በእግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎችም የሚፈተኑት በውርደት ምድጃ ነው። 6 በእግዚአብሔር ታመን፥ ይረዳሃል፤ ትክክለኛውን መንገድ ተከተል፤ ተስፋህም በእርሱ ላይ ይሁን፤ 7 እናንተ ጌታን የምትፈሩ ምሕረቱን ተጠባበቁ፤ እንዳትወድቁ ከሱ አትራቁ። 8 እናንተ ጌታን የምትፈሩ በሱ ተማመኑ፤ የሚገባችሁ ዋጋ አይቀርባችሁም፤ 9 እናንተ ጌታን የምትፈሩ፥ የእርሱን መልካም ስጦታዎች ደስታንና ምሕረትን ተስፋ አድርጉ። 10 ያለፉትን ትውልዶች ተመልከቱ፥ እዩ፤ እስቲ ማነው በጌታ ተማምኖ ያፈረ? 11 ማነው እግዚአብሔርን በመፍራት ጸንቶ የተጣለ? ማነው እግዚአብሔርን ለምኖ ያልተሰማ? ምክንያቱም እግዚአብሔር ርኁርኀና መሐሪ ነው፤ ኃጢአትን ይቅር የሚልና በጭንቀት ጊዜ የሚያድን ነው። 12 ስንፍና ለሚያጠቃቸው ልቦችና፥ ብርታት ለሌላቸው እጆች ወዮላቸው፤ በሁለት መንገድ የሚሄድ ወላዋይ ኃጢአተኛ ወዮለት። 13 ብርታትና እምነት የሌለው ልብ ወዮለት፤ ምክንያቱም ጠባቂ የለውም። 14 እናንተ ጸንታችሁ ያልኖራችሁ ወዮላችሁ፤ ጌታ ሲጐበኛችሁ ምን ልታደርጉ ነው? 15 ጌታን የሚፈሩ ሰዎች፤ ከቶ ቃሉን አይጥሱም፤ እግዚአብሔርን የሚወዱ መንገዶችን ይጠብቃሉ፤ 16 ጌታን የሚፈሩ ሁሉ፥ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ይፈጽማሉ፤ እሱን የሚወዱ በሕጉ ይረካሉ። 17 ጌታን የሚፈሩ ሁልጊዜ ዝግጁ ልብ አላቸው፤ በፊቱ ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፤ እንዲህም ይላሉ፥ 18 በሰው እጅ ከምንወድቅ በእርሱ እጅ እንውደቅ፤ ምሕረቱ እንደ ታላቅነቱ ነውና። |