Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 42 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የተቀደሱት ክፍሎችና የውጭው ግንብ

1 በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጪው አደባባይ አወጣኝ፥ በተለየው ስፍራ ፊት ለፊት፥ በሰሜን በኩል ባለው ህንጻ ፊት ለፊት ወዳለው ክፍል አገባኝ።

2 በሰሜን በኩል ያለው መግቢያ ርዝመት መቶ ክንድ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ።

3 በውስጠኛው አደባባይ በሀያው ክንድ ፊት ለፊት በውጭውም አደባባይ በወለሉ ፊት ለፊት በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ።

4 ከክፍሎቹም ፊት ለፊት በውስጥ በኩል ወርዱ ዐሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መግቢያዎቹም በሰሜን በኩል ነበሩ።

5 መተላለፊያው አሳጥሮአቸዋልና የላይኞቹ ክፍሎች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ።

6 በሦስት ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩአቸውም፥ ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ።

7 በክፍሎቹ ትይዩ በውጭ ያለው ቅጥር፥ በክፍሎቹ ፊት ለፊት ያለው የውጭው አደባባይ ርዝመት አምሳ ክንድ ነበረ።

8 በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ክፍሎች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ሲሆን በመቅደሱ ፊት ለፊት የነበሩት ክፍሎች ግን ርዝመታቸው መቶ ክንድ ነበረ።

9 ከእነዚህም ክፍሎች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባባት መግቢያ ነበረ።

10 በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ግንብ ርዝመት፥ በተለየው ስፍራና በሕንጻው ፊት ለፊት ክፍሎች ነበሩ።

11 በፊታቸው የነበረው መንገድም በሰሜን በኩል ያሉትን ክፍሎች ይመስል ነበር። ርዝመታቸውም፥ ወርዳቸውም፥ መውጫቸውም አቀማመጣቸውና መግቢያዎቻቸውም ተመሳሳይ ነበር።

12 በደቡብም በኩል ካሉት ክፍሎች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ።

13 እንዲህም አለኝ፦ በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ ጌታ የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቁርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ።

14 ካህናቱም ከገቡ በኋላ የሚያገለግሉበትን ልብስ ሳያወልቁ ከመቅደሱ ወደ ውጭው አደባባይ አይወጡም፥ የተቀደሱ ናቸውና፤ ወደ ሕዝቡ ቦታ ሲቀርቡ ሌላ ልብስ መልበስ አለባቸው።

15 ውስጠኛውን ቤት ለክቶ ሲጨርስ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ፥ ዙሪያውን ሁሉ ለካ።

16 በምሥራቅ አቅጣጫ ያለውን በመለኪያ ዘንግ ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ።

17 በሰሜን አቅጣጫ ያለውን ለካ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ።

18 በደቡብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ።

19 በምዕራብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ።

20 በአራቱ አቅጣጫ ለካ፤ የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ለመለየት ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።

跟着我们:



广告