本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሰባት ወንድማማቾች ሰማዕትነት 1 እንዲሁም ሰባት ወንድማማቾች ከእናታቸው ጋር ተያዙና ታሰሩ። ንጉሡ በጅራፍና በበሬ ጅማት እያስገረፈ በሕግ የተከለከለውን የዓሣማ ሥጋ እንዲቀምሱ አስገደዳቸው። 2 ከእነሱ አንዱ በወንድሞቹ ስም፥ “ከእኛ ምን ትጠይቃለህ፥ ምንስ ማወቅ ትፈለጋለህ? የአባቶቻችንን ሕግ ከማፍረስ መሞትን እንመርጣለን” አለ። 3 ንጉሡ በጣም ተቆጥቶ ብረት ምጣድና ብረት ድስት በእሳት እንዲያግሉ አዘዘ። 4 ብረት ምጣዱና ብረት ድስቱ በጣም በጋሉ ጊዜ ንጉሡ ያን በወንድሞቹ ስም የተናረገውን ሰው ምላሱ እንዲቆረጥ፥ የራስ ቅሉ ቆዳ እንዲገፈፍ፥ በወንድሞቹና በእናቱ ፊት እጆቹና እግሮቹ እንዲቆረጡ አዘዘ። 5 በሙሉ ከቆራረጡት በኋላ ገና በሕይወቱ እያለ በብረት መጣድ ላይ አድርገው አንዲጠብሱት አዘዘ፤ ከጋለው ብረት ምጣድ ላይ ጭሱ ሲወጣ ሳለ ወንድሞቹና እናቱ ያለ ፍርሃት ለመሞት ይመካከሩ ነበር፤ እንዲህም ይሉ ነበር፤ 6 “እግዚአብሔር አምላክ ያያል፤ ሙሴ እንደተናረገው በእውነት ይራራልናል፤ ሙሴ እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ ይራራላቸዋል ሲል መስክሮአልና”። 7 የመጀመሪያው እንዲህ ሆኖ ከሞተ በኋላ ሁለተኛውን ወደሚያሠቃዩበት ቦታ ወሰዱት፤ 8 የራስ ቅሉን ቆዳ ከነጠጉሩ ገፍፈው ከጣሉ በኋላ “የአካልህ ክፍሎች እያንዳንዱ ከሚበሠቃዩ የዓሣማ ሥጋ ትበላለህን?” ሲሉ ጠየቁት። 9 እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አድርጐ ተናገረ፥ “ጨካኝ አውሬዎች ከዚህ ከአሁኑ ሕይወት ትገላግሉን ይሆናል፤ የዓለም ጌታ ግን ስለ ሕጎቹ በመሞታችን ለዘለዓለም እንኖር ዘንድ ያስነሣናል”። 10 ከእርሱ በኋላ ሦስተኛውን አሠቃዩት፥ ምላስህን አውጣ ሲሉት በቶሎ አወጣ እጆቹንም ያለ ምንም ፍርሃት ዘረጋላቸው። 11 “እነርሱን የሰጠኝ አምላክ ነው፤ ስለ ሕጉ ስል እንቃቸዋለሁ፤ ከእርሱ እንደገና መልሼ ላገኛቸው ተስፋ አለኝ” አላቸው። 12 ንጉሡና ከንጉሡ ጋር የነበሩት ሰዎች ሥቃዩን ሁሉ ከምንም በማይቆጥረው በእዚህ ወጣት ብርታት ተደነቁ፤ 13 ይህ ከሞተ በኋላ አራተኛውንም በተመሳሳይ ሁኔታ አሠቃዩት፤ 14 እርሱ ሊሞት ሲል እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ መሠረት በእርሱ ከሞት የምነነሣ መሆናችንን በመጠባበቅ በሰው እጅ መሞት የተሻለ ነው፤ አንተ ግን ከሞት በሕይወት አትነሣም”። 15 ቀጥሎ አምስተኛውን አመጡና አሠቃዩት፤ 16 እርሱ ግን ንጉሡን ትኩር ብሎ እያየ እንዲህ አለ፥ “አንተ ምንም ሟች፥ በስባሽ ብትሆን ሥልጣን አለህ፤ የፈለግኸውንም ማድረግ ትችላለህ፤ ግን ዘራችን በእግዚአብሔር የሚጣል አይምሰልህ። 17 አንተ ግን ጠብቅ፥ ታላቅ ሥልጣኑን ታያለህ፤ አንተን ከነዘርህ ያሠቃይሀል”። 18 ከእርሱ በኋላ ስድስተኛውን አመጡ፤ እርሱም ሊሞት ሲል እንዲህ አለ፥ “በከንቱ አትሳሳት፤ በአምላካችን ላይ ኃጢአት ስለሠራን እኛ ስለእራሳችን ነው የምንሠቃየው፤ ይህ መጥፎ ዕድል የወደቀብን ስለዚህ ነው፤ 19 ከእግዚአብሔር ጋር የምትዋጋ አንተ ግን ቅጣትንህን ሳትቀበል የምትቀር አይምስልህ”። 20 እጅግ የምታስደንቅና ትውስታዋ የማይጠፋው እናትየዋ ናት፤ እርሷ ሰባቱም ልጆችዋ በአንድ ቀን ሲሞቱ እያየች ጸጥ ብላ ታገሰች፤ ምክንያቱም ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ጥላ ስለ ነበር ነው። 21 ልጆችዋን በአባቶችዋ ቋንቋ ትመክራቸው ነበር፤ በታላቅ እምነትም የሴትነት ክርክሯን በተባዕት ድፍረት በማጽናት እንዲህ አለቻቸው፥ 22 “ማሕፀኔ እንዴት እንደተፈጠራችሁ አላውቅም፤ እስትንፋስና ሕይወት የሰጠኋችሁ እኔ አይደለሁም፤ የእያንዳንዳችሁን አካል የሠራሁት እኔ አይደለሁም። 23 ሰውን ገና ሲወለድ የፈጠረና ከሁሉ ነገር በፊት የነበረ የዓለም ፈጣሪ በምሕረቱ መንፈስንና ሕይወትን ይሰጣችኋል፤ ምክንያቱም ስለ ሕጎቹ ስትሉ ለሕይወታችሁ አልሳሳችሁምና”። 24 አንጥዮኩስ የተናቀ መሆኑን አሰበና እነዚህ ቃሎች የውርደት ሳይሆን አይቀሩም በማለት ተጠራጠረ። የሁሉም ታናሽ ቀርቶ ነበር፤ እርሱን በምክር ተናረገው፤ እንዲሁም የአባቶቹን ባህል የተወ እንደሆነ ባለጠጋና ደስተኛ እንደሚያደርገው በመሐላ አረጋገጠለት፤ ወዳጁ እንደሚያደርገውና ከፍ ያለ ሹመት እንደሚሰጠው ነገረው፤ 25 ወጣቱ ልጅ ነገሩን ስላልተቀበለው ንጉሡ እናቱን ጠራና ልጅሽ ሕይወቱን እንዲያድን ምክሪው አላት፤ 26 ንጉሡ ብዙ ከመከራት በኋላ እሺ ልጁን ላሳምነው እሞክራለሁ አለች፤ 27 ስለዚህ ወደ ልጇ ጐንበስ አለችና በንጉሡ እያላገጠች በአባቶዋ ቋንቋ እንዲህ ስትል ተናገረች፤ “ልጄ ሆይ ዘጠኝ ወር በማሕፀኔ ለተሸከምሁህ ራራልኝ፤ ሦስት ዓመት አጠባሁህ፤ አሁን እስካለህበት ዕድሜ ድረስ እየመገብሁ አሳደግሁህ፤ ምንም ሳይጐድልህ ለዚህ አደረስኩህ። 28 የእኔ ልጅ አደራ እያልሁ እለምንሃለሁ፤ ሰማይና ምድርን ተመልከት፤ በእነርሱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ህልው ካልሆነ ነገር የፈጠራቸው መሆኑን ዕወቅ፤ የሰው ዘርም የተፈጠረው እንዲሁ ነው። 29 ልጄ ሆይ ይህን ነፍሰ ገዳይ አትፍራ፤ በምሕረት ቀን ከወንድሞችህ ጋር እንዳገኝህ እንደወንድሞችህ በክብር ሙት”። 30 እርሷ ንግግሯን እንደጨረሰች ወዲያውኑ ወጣቱ እንዲህ አለ፥ “ምን ትጠብቃላችሁ? የንጉሡን ትእዛዝ አልቀበልም፤ በሙሴ ለአባቶቻችን የተሰጠውን አከብራለሁ፤ 31 አንተ በዕብራውያን ላይ ይህን መከራ ያመጣህ ከእግዚአብሔር እጅ አታመልጠም፤ 32 ምክንያቱም እኛ የምንሠቃየው በኃጢአታችን ምክንያት ነው። 33 አዎ እኛን ለመቅጣትና ለመገሠጽ ሕያው የሆነው አምላካችን በእኛ ላይ ተቆጣ፤ ከአገልጋዮቹ ጋር እንደገና ይታወቃል። 34 አንተ ግን ከሰው ሁሉ ይብስ የከፋህ ኃጢአተኛ በከንቱ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ እጅህን በማንሣት በከንቱ አትታበይ፤ 35 ምክንያቱም አንተ ሁሉን ከሚችልና ሁሉን ከሚያይ አምላክ ፍርድ ገና አላመለጥህም። 36 አሁን ለሚያልፈው ሕይወት ሲሉ የሚያልፈውን ሥቃይ የተቀበሉ ወንድሞቻችን ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሲሉ ወደቁ (ሞቱ)፤ አንተ ግን በእግዚአብሔር ፍርድ ስለ ትዕቢትህ የተነገባውን ቅጣት ታገኛለህ። 37 እኔም እንደ ወንድሞቼ ስለ አባቶቼ ሕግ ሥጋዬንና ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እግዚአብሔር ለሕዝባችን ቶሎ እንዲራራና አንተንም በፈተናና በመቅሠፍት እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑን ለማወቅ እንዲያስችልህ እለምነዋለሁ፤ 38 ሁሉን የሚችል አምላክ በቅን ፍርዱ በዘራችን ላይ ያወረደው መዓት በእኔና በወንድሞቼ እንዲቆም እለምነዋለሁ”። 39 ይህ ወጣት ስላላገጠበት ከሌሎቹ ይበልጥ የንጉሡ መዓት ወረደበት። 40 ወጣቱ ሳያድፍ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ጥሎ ሞተ። 41 በመጨረሻም ከልጆችዋ በኋላ እናትዬዋ ሞተች። 42 ስለ አምልኮ መብልና ስለ አስፈሪው ሥቃይ የምንለውን በዚሁ እናበቃለን። |