本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአሕዛብን አምልኮ በግዳጅ ማስፈን 1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ አይሁዳውያን ከአባቶቻቸው ሕግ እንዲርቁና ሕይወታቸውንም በእግዚአብሔር ሕግ መምራቱን እንዲያቋርጡ ለማድረግ ጀሮንቲስን የተባለውን አንድ አቴናዊ ላከባቸው፤ 2 የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ለማርከስና የኦሎምፖያው ዜኦስ እንዲከብር ለማድረግ በጌሪዝም ተራራ ላይ የዜኦስ የእንግዶች ጠባቂ መታሰቢያ ለማቆም አቴናውያን በጠየቁት መሠረት ወሰነ። 3 የእዚህ እርኩስ ተግባር መታየት ሕዝቡ ሊሸከመው ከማለው በላይ ስቃይን አስከተለ። 4 ቤተ መቅደሱ ቅጥ ባጣ ደስታና በጭፈራ ተሞላ፤ አረማውያን ከሴቶች ጋር የሚዳሩበትም ቦታ ሆነ። የተከለከለ ነገርም ይፈጽሙ ነበር። 5 መሠዊያውም በሕግ በተከለከሉና በረከሱ መሥዋዕቶች ተሞልቶ ነበር፤ 6 ሰንበትን ማክበር አልተፈቀደም ነበር፤ ሃይማኖታዊ በዓላትን ማሰብ፥ ሌላው ቀርቶ አይሁድ ነኝ ብሎ መናገርም አይፈቀድም ነበር። 7 በንጉሡ የልደት በዓል ቀን በየወሩ እየሄዱ መብላት የማይታለፍ ግዴታ ነበር፤ የዲዮንስዩስ በዓል በሆነ ጊዜ በራስ ላይ የቅጠል ጉንጉን ደፍቶ የዲዩንስዩስን ሰልፍ መከተል ግዴታ ነበር። 8 በጰጠሎማይዳ ሰዎች ምክር በአረማውየን (ግሪካውያን) ከተሞች አጠገብ የሚገኙ አይሁዳውያን እንደ አረማውያን እንዲያደርጉ አዋጅ ወጣ፤ አይሁዳውያንም ለመሥዋዕት የቀረበውን ምግብ እንዲበሉ ተገደዱ፤ 9 የግሪካውያንን ልምድ የማይከተሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ ተሰጠ። በዚያን ጊዜ እንግዲህ ታላቅ ችግር የሚመጣ መሆኑ ታወቀ። 10 ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ስላስገረዙ በፍርድ ፊት አቀረቧቸው፤ በሰው ሁሉ ፊት ልጆቻቸውን እንደታቀፉ ከተማውን እንዲዞሩ ተደረጉ፤ ከዚህም በኋላ በግንቡ ላይ ወርውረው ጣሏቸው። 11 ሌሎች በድብቅ የሰንበትን በዓል ለማክበር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ዋሻዎች አብረው ሄዱ። በፊሊጶስ ፊት ተከሰው በእሳት አቃጠሏቸው፤ ለቀኑ ክብር ካላቸው የእምነት ጽናት የተነሣ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ። በድኀንነት ጐዳና የስደት አስፈላጊነት 12 ይህን መጽሐፍ የሚያነቡ ሰዎች በእነዚህ መከራዎች ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ አደራ እላለሁ፤ ይህ ስደት ለሕዝባችን ተግሣጽ፤ ትምህርት እንጂ ጥፋት አለመሆኑን እንዲገነዘቡ እለምናለሁ። 13 ክፉ ሰዎች በክፋታቸው ረጅም ጊዜ ባለመቆየታቸው፥ ቅጣታቸውም ቶሎ የሚደርስባቸው በመሆኑ የእግዚአብሔር ታላቅ ደግነት ምልክት ነው። 14 ልዑል አምላክ ሌሎችን ሕዝቦች ለመቅጣት የክፋታቸው ጽዋ እስኪሞላ ድረስ በምሕረቱ ታግሦ ይጠብቃቸዋል። ግን ከእኛ ጋር የሚያደርገው እንዲህ አይደለም፤ 15 እኛን የሚቀጣን ኃጢአታችን እስከ መጨረሻ ሳይሞላ ነው። 16 ስለዚህ ምሕረቱን ከቶ ከእኛ አያርቅም፤ መከራ አውርዶብን ቢገሥጸንም እኛን ሕዝቡን አይጥለንም። 17 ይህን ማስታወስ ይበቃል፤ ከእዚህ በኋላ ወደ ነገራችን እንመለስ። የአልዓዛር ሰማዕትነት 18 የሕግ ሊቃውንት ከነበሩት አንዱ የሆነውንና በዕድሜ የገፋ በሁሉም ዘንድ የተከበረ አልዓዛር የተባለውን ሰው አፍ በግድ ከፈተው የዓሣማ ሥጋ እንዲበላ አስገደዱት። 19 እርሱ ግን ከወራዳ ሕይወት የክብረ ሞት ይሻለኛል ብሎ 20 ያልተፈቀደ ነገርን መቅመስ እንደሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ በአፉ ውስጥ የገባውን ቁራጭ ሥጋ በመትፋት ከሕይወት ይልቅ ሞትን መረጠ። በገዛ ፈቃዱ ወደሚያሠቃዩበት ቦታ ሄደ። 21 በበዓሉ ላይ የነበሩ ሰዎች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ አልዓዛርን ያውቁት ስለ ነበር ገለል አደረጉትና ለመኑት፤ እርሱ መብላት የሚችለውን ሥጋ ከገዛ ቤቱ እንዲያስመጣና በንጉሡ እንደ በላ የታዘዘውን ሥጋ አሥመስሎ እንዲበላ መከሩት፤ 22 እንዲህ በማድረግ ከሞት ስለሚድን በቀድሞ ፍቅራቸው ምክንያት ይህን መከሩት። 23 እርሱ ግን ለዕድሜው የተስማማ የክብር ሥራ ለመሥራት ፈልጐ ከልጅነቱ ጀምሮ ሳያወላውል የኖረ፤ ይልቁንም በተቀደሰው የእግዚአብሔር ሕግ የጸና፤ በተከበረ ሸምግልናውና ሽበቱ ሥልጣን ያለው መሆኑን አውቆ ሳትዘገዩ ግደሉኝ ሲል መልስ ሰጠ፤ 24 እንዲህም አለ፥ “በእኛ ዕድሜ በማስመሰል መሥራት አይገባም፤ አለበለዚያ ወጣቶች ለዚች ዕድሜው ሲል አልዓዛር በዘጠና ዓመት ዕድሜው የሌሎችን አገሮች ሕይወት ተከተለ ብለው ያምናሉ፤ 25 ታዲያ እነርሱም ለብዙ ጊዜ በማይጠቅመኝ በዚህ ወራዳ ድርጊት የተነሣ አኔን በመመልከት ከሚከተሉት ቀና ጐዳና ሊወጡ ይችላሉ። በስተርጅና ላተርፍ የምችለው ነገር ቢኖር እራሴን ማሳደፍና ክብሬን ማዋረድ ብቻ ነው። 26 አምላክ እጅ አላመልጥም። 27 አሁን ምንም ሳልፈራ ሕይወቴን አሳልፌ ብሰጥ ለሽምግልናዬ የተገባሁ ሆኜ እገኛለሁ፤ 28 ይህን በማድረጌ ወጣቱ ትውልድ በደግነት፥ በክብርና በጉጉት ስለቅዱሳት ሕግጋት ሲል ሞትን በድፍረት ይጋፈጥ ዘንድ የእኔን አብነት ይከተላል”። 29 ይወስዱት የነበሩ ሰዎች በፊት በመልካም ዐይን ይመለከቱት የነበሩ ሐሳባቸውነ ለውጠው በክፉ ዐይን ተመለከቱተ፤ ምክንያቱም የተናገረው ንግግር እንደ ዕብደት መስሎ ታያቸው። 30 እርሱ ግን ሲደበደብ ሳለ ከመሞቱ በፊት እየሳቀ እንዲህ አለ፥ “ቅዱስ ዕውቀት ያለው አምላክ ከሞት ማምለጥ ስችል በሥጋዬ የሚያሠቃዩኝን ጅራፎች ታግሼ መቀበሌን ያውቃል፤ ነገር ግን ነፍሴ ይህን ሁሉ ስቃይ በመቀበል ትደሰታለች”። 31 በእንደዚህ ዓይነት ነው ይህ ሰው በሞቱ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለሕዝቦች ሁሉ የጥንካሬ ምሳሌና የብርታት ማስታወሻ ትቶ ያለፈው። |