ኢያሱ 20 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት)1 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2-3 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ሳይወድድ ሳያውቅም ሰውን የገደለ ገዳይ እንዲሸሽባቸው በሙሴ እጅ የነገርኋችሁን መማፀኛ ከተሞችን ለዩ፥ ከደም ተበቃዩ መማፀኛ ይሆኑላችኋል። 4 ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ይሸሻል፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሞ በከተማይቱ ሽማግሌዎች ጆሮ ነገሩን ይናገራል፥ እነርሱም ወደ ከተማይቱ ይቀበሉታል፥ የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል። 5 ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን በስሕተት ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። 6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፥ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፥ ወደ ከተማውም ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣበትም ከተማ ይገባል። 7 በንፍታሌም ባለው በተራራማው አገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው አገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው አገር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያትአርባቅን ለዩ። 8 በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ራሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። 9 በማኅበሩ ፊት እስኪቆም ድረስ በደም ተበቃዩ እጅ እንዳይሞት ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመካከላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተለዩ ከተሞች እነዚህ ናቸው። |