Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ሳሙኤል 18 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት)

1 ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው።

2 ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሢሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን፦ እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው።

3 ሕዝቡ ግን፦ አትወጣም፥ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፥ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፥ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአሥሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፥ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ።

4 ንጉሡም፦ መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ።

5 ንጉሡም ኢዮአብንና አቢሳን ኢታይንም፦ ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለ አቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ።

6 ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ሰልፉም በኤፍሬም ዱር ውስጥ ሆነ።

7 በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሀያ ሺህ ሰውም ሞተ።

8 ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፥ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ።

9 አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፥ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፥ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ።

10 አንድ ሰውም አይቶ፦ እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው።

11 ኢዮአብም ለነገረው ሰው፦ እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አሥር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው።

12 ሰውዮውም ኢዮአብን፦ እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም፦ ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር አለው።

13 እኔ ቅሉ በነፍሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሣህብኝ ነበር አለው።

14 ኢዮአብም፦ እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው።

15 አሥሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት።

16 ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ።

17 አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፥ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

18 አቤሴሎምም ሕያው ሳለ፦ ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፥ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል።

19 የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ግን፦ እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ።

20 ኢዮአብም፦ በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፥ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው።

21 ኢዮአብም ኵሲን፦ ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነሥቶ ሮጠ።

22 ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን፦ የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም፦ ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ።

23 እርሱም፦ እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም፦ ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንገድ በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው።

24 ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፥ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደበሩ ሰገነት ወጣ፥ አይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ።

25 ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም፦ ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ።

26 እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፥ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ፦ እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም፦ እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ።

27 ዘበኛውም፦ የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፥ ንጉሡም እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካም ወሬ ያመጣል አለ።

28 አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን፦ ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፦ በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።

29 ንጉሡም፦ ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም፦ ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት።

30 ንጉሡም፦ ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፥ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ።

31 እነሆም፥ ኵሲ መጣ፥ ኵሲም፦ እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደ ተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቼአለሁ አለ።

32 ንጉሡም ኵሲን፦ ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን? አለው። ኵሲም፦ የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት።

33 ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፥ ሲሄድም፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር።

跟着我们:



广告