Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ሳሙኤል 1 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት)

1 እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ።

2 በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፥ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ።

3 ዳዊትም፦ ከወዴት መጣህ? አለው፥ እርሱም፦ ከእስራኤል ሰፈር ኮብልዬ መጣሁ አለው።

4 ዳዊትም፦ ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ፦ ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፥ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ።

5 ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው።

6 ወሬኛውም ጕልማሳ አለ፦ በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ቆሞ ነበር፥ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት።

7 ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፥ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ።

8 እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፥ እኔም፦ አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት።

9 እርሱም፦ ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ።

10 እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፥ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት።

11 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ።

12 በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ።

13 ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ አንተ ከወዴት ነህ? አለው፥ እርሱም፦ እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት።

14 ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው።

15 ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፦ ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም።

16 ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው።

17 ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኅዘን ቅኔ ተቀኘ፥

18 የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።

19 የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፥ ኃያላን እንዴት ወደቁ!

20 የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቆላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፥ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ።

21 እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ።

22 ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም።

23 ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፥ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፥ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፥ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።

24 የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት።

25 ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል።

26 ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፥ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበር፥ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ።

27 ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!

跟着我们:



广告