2 ነገሥት 9 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት)ኢዩ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ 1 ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው “ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ማሰሮ በእጅህ ያዝ፤ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ። 2 በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፤ ወደ ጓዳም አግባው። 3 የዘይቱንም ማሰሮ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤” በለው፤’ በሩንም ከፍተህ ሽሽ፤ አትዘግይም።” 4 እንዲሁም ጐልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ። 5 በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “አለቃ ሆይ! ለአንተ መልእክት አለኝ፤” አለ። ኢዩም “ለማንኛችን ነው?” አለ። እርሱም “አለቃ ሆይ! ለአንተ ነው፤” አለ። 6 ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ። 7 የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። 8 የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል፤ በእስራኤልም ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ ከአክዓብ አጠፋለሁ። 9 የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10 ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፤ የሚቀብራትም አታገኝም።’” በሩንም ከፍቶ ሸሸ። 11 ኢዩም ወደ ጌታው አገልጋዮች ወጣ፤ እነርሱም “ደኅና ነውን? ይህ እብድ ለምን መጣብህ?” አሉት። እርሱም “ሰውዮውንና ንግግሩን ታውቃላችሁ፤” አላቸው። 12 እነርሱም “ሐሰት ነው፤ ያለውን ንገረን፤” አሉት፤ እርሱም “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤’ ብሎ እንዲህ እንዲህ ነገረኝ፤” አላቸው። 13 ሁሉም ፈጥነው ልባሳቸውን ወሰዱ፤ በሰገነቱ መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት፤ ቀንደ መለከትም እየነፉ፥ “ኢዩ ነግሦአል!” አሉ። የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም እንደ ተገደለ 14 እንዲሁም የናሜሲ ልጅ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ ተማማለ። ኢዮራምና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል የተነሣ ሬማት ዘገለዓድን ይጠብቁ ነበር። 15 ንጉሡ ኢዮራም ግን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም “ልባችሁስ ከእኔ ጋር ከሆነ በኢይዝራኤል እንዳያወራ ማንም ከከተማ ኮብልሎ አይውጣ፤” አለ። 16 ኢዮራምም በዚያ ታምሞ ተኝቶ ነበርና ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮራምን ለማየት ወርዶ ነበር። 17 በኢይዝራኤልም ግንብ ላይ የቆመው ሰላይ የኢዩ ጭፍራ ሲመጣ አይቶ “ጭፍራ አያለሁ፤” አለ። ኢዮራምም “የሚገናኘው ፈረሰኛ ላክ፤ እርሱም ‘ሰላም ነውን?’ ይበለው፤” አለ። 18 ፈረሰኛውም ሊገናኘው ሄዶ “ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘ሰላም ነውን?’” አለ። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ፤” አለ። ሰላዩም “መልእክተኛው ደረሰባቸው፤ ነገር ግን አልተመለሰም፤” ብሎ ነገረው። 19 ሁለተኛም ፈረሰኛ ሰደደ፤ ወደ እነርሱም ደርሶ “ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘ሰላም ነውን?’” አለ። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ፤” አለ። 20 ሰላዩም “ደረሰባቸው፤ ነገር ግን አልተመለሰም፤ በችኮላ ይሄዳልና አካሄዱ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አካሄድ ነው፤” ብሎ ነገረው። 21 ኢዮራምም “ሠረገላ አዘጋጁ፤” አለ፤ ሠረገላውንም አዘጋጁለት። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮራም የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ በሠረገሎቻቸው ተቀምጠው ወጡ፤ ኢዩንም ሊገናኙት ሄዱ፤ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ውስጥ አገኙት። 22 ኢዮራምም ኢዩን ባየ ጊዜ “ኢዩ ሆይ! ሰላም ነውን?” አለ። እርሱም “የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተትዋ ሲበዛ ምን ሰላም አለ?” ብሎ መለሰ። 23 ኢዮራምም መልሶ ነዳና ሸሸ፤ አካዝያስንም “አካዝያስ ሆይ! ዓመፅ ነው፤” አለው። 24 ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ፤ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ፤ ወደ ሠረገላውም ውስጥ ወደቀ። 25 ኢዩም አለቃውን ቢድቃርን እንዲህ አለው “አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ጣለው፤ አንተና እኔ ጎን ለጎን በፈረስ ተቀምጠን አባቱን አክዓብን በተከተልን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይህን መከራ እንደ ተናገረበት አስብ፤ 26 ‘በእውነት የናቡቴንና የልጆቹን ደም ትናንትና አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚህም እርሻ እመልስብሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ወስደህ በእርሻው ውስጥ ጣለው።” የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ እንደ ተገደለ 27 የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ያንን ባየ ጊዜ በአትክልት ቤት መንገድ ሸሸ። ኢዩም “ይህን ደግሞ በሠረገላው ላይ ውጉት፤” እያለ ተከተለው፤ በይብለዓምም አቅራቢያ ባለችው በጉር ዐቀበት ላይ ወጉት። ወደ መጊዶም ሸሸ፤ በዚያም ሞተ። 28 ባሪያዎቹም በሠረገላው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ በመቃብሩ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። 29 በአክዓብም ልጅ በኢዮራም በዐሥራ አንደኛው ዓመት አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ። የንግሥት ኤልዛቤል መገደል 30 ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል መጣ፤ ኤልዛቤልም በሰማች ጊዜ ዐይንዋን ተኳለች፤ ራስዋንም አስጌጠች፤ በመስኮትም ዘልቃ ትመለከት ነበር። 31 ኢዩም በበሩ ሲገባ “ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሆይ! ሰላም ነውን?” አለችው። 32 ፊቱንም ወደ መስኮቱ አንሥቶ “ከእኔ ጋር ማን ነው?” አለ። ሁለት ሦስትም ጃንደረቦች ወደ እርሱ ተመለከቱ። 33 እርሱም “ወደ ታች ወርውሩአት፤” አለ፤ ወረወሩአትም፤ ደምዋም በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ፤ ረገጡአትም። 34 በገባም ጊዜ በላ ጠጣም፤ ከዚያም በኋላ “ይህችን የተረገመች እዩ፤ የንጉሥ ልጅ ናትና ቅበሩአት፤” አለ። 35 ሊቀብሩአትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍም በቀር ምንም አላገኙም። 36 ተመልሰውም ነገሩት፤ እርሱም “በባሪያው በቴስብያዊ ኤልያስ ‘በኢይዝራኤል እርሻ የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ፤ 37 የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል እርሻ መሬት ላይ እንደ ፍግ ይሆናልና ማንም “ይህች ኤልዛቤል ናት፤” ይል ዘንድ አይችልም፤’ ብሎ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤” አለ። |