Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ሳሙኤል 24 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት)

1 እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፦ እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት።

2 ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ።

3 በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፥ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር።

4 የዳዊትም ሰዎች፦ እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገርህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቆረጠ።

5 ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቆረጠ የዳዊት ልብ በኅዘን ተመታ።

6 ሰዎቹንም፦ እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው።

7 ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፥ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ።

8 ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፥ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጎንብሶ እጅ ነሣ።

9 ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ?

10 እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፥ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተንገሩኝ፥ እኔ ግን፦ በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ።

11 ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፥ የልብስህንም ዘርፍ በቆረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፥ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ።

12 እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፥ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።

13 በጥንት ምሳሌ፦ ከኃጢአተኞች ኃጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፥ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።

14 የእስራኤል ንጉሥ ማንም ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን?

15 እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ።

16 እንዲህም ሆነ፥ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል፥ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፥ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

17 ዳዊትን አለው፦ እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።

18 እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ።

19 ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ።

20 አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ።

21 አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቆርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ።

22 ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፥ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ።

跟着我们:



广告