አብድዩ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በኤዶምያስ ላይ የሚደርስ ቅጣት 1 የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ መስማትን ሰማሁ፤ ከባቢን ወደ አሕዛብ ልኮ፥ “ተነሡ፤ በላይዋም እንነሣና እንውጋት። 2 እነሆ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፤ አንተ እጅግ ተንቀሃል። 3 በተሰነጠቀም ዓለት ውስጥ እንደሚኖር- ማደሪያውንም ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ፥ በልቡም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? እንደሚል፥ የልብህ ትዕቢት እጅግ አኵርቶሃል። 4 እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። 5 “ሌቦች ቢመጡብህ፥ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን? 6 ዔሳውን እንዴት መረመሩት! የሸሸገውንም እንዴት ወሰዱበት! 7 የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፤ የተስማሙህም ሰዎች ተነሡብህ፤ አሸነፉህም፤ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፤ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። 8 በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳው ተራራም ማስተዋልን አጠፋለሁ ይላል እግዚአብሔር። 9 ከዔሳው ተራራ ሰዎች ሁሉ ይጠፉ ዘንድ የቴማን ሰልፈኞችህ ይደነግጣሉ። 10 “በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ኀጢአትና ግድያ ኀፍረት ይከድንሃል፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። 11 በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ። 12 በጠላት ቀን ወንድምህን ዝቅ አድርገህ ትመለከተው ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ ባልተገባህ ነበር። 13 በችግራቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጉባኤያቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በእልቂታቸውም ቀን በሠራዊታቸው ላይ አደጋ ትጥል ዘንድ አይገባህም ነበር። 14 የሸሹትንም ለማጥፋት በመተላለፊያ መንገዳቸው ትቆም ዘንድ፥ ድል በተነሡበትም ቀን ከእርሱ ያመለጡትን ለማስጨነቅ ትከብባቸው ዘንድ ባልተገባህ ነበር። እግዚአብሔር በአሕዛብ እንደሚፈርድ 15 “የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፥ አንተ እንደ አደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፤ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። 16 በቅዱሱ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣህ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ወይንን ይጠጣሉ፤ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፤ እንዳልነበሩም ይሆናሉ። የእስራኤል ድል 17 “ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ መድኀኒት ይሆናል፤ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች የወረሱአቸውን ይወርሳሉ። 18 እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍም ቤት ነበልባል፥ የዔሳውም ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል፤ ይበሉአቸውማል፤ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ አይኖርም። 19 የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥኤማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም ተራራ፥ የሰማርያን፥ የብንያምንና የገለዓድን ሀገር ይወርሳሉ። 20 ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፤ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች እስከ ኤፍራታ ድረስ የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። 21 የዳኑትም የዔሳውን ተራራ ይበቀሉት ዘንድ ከጽዮን ተራራ ይዘምታሉ፤ መንግሥትም ለእግዚአብሔር ይሆናል።” |