መሳፍንት 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አቤሜሌክ 1 የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሰቂማ ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፤ ለእነርሱም፥ ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 2 “ለሰቂማ ሰዎች ሁሉ፦ ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው፤ ደግሞም እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ፥ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ።” 3 የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሰቂማ ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፤ እነርሱም፥ “እርሱ ወንድማችን ነው” ብለው ልባቸውን ወደ አቤሜሌክ መለሱት። 4 ከበዓልም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ወንበዴዎችንና አስደንጋጮችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከትለውት ሄዱ። 5 ወደ አባቱም ቤት ወደ ኤፍራታ ገባ፤ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ። 6 የሰቂማም ሰዎች ሁሉ፥ የመሐሎንም ቤት ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ሄደውም በሰቂማ በዐምዱ አጠገብ ባለው የወይራ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ። 7 ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፤ ድምፁንም አንሥቶ አለቀሰ፤ እንዲህም አላቸው፥ “የሰቂማ ሰዎች ሆይ! ስሙኝ እግዚአብሔርም ይስማችሁ። 8 አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ፤ ወይራንም፦ በእኛ ላይ ንገሺልን አሉአት። 9 ወይራዋ ግን፦ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያከብርበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን? አለቻቸው። 10 ዛፎችም በለሲቱን፦ መጥተሽ በላያችን ንገሺልን አሉአት። 11 በለሷ ግን፦ ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እነግሥ ዘንድ ልሂድን? አለቻቸው። 12 ዛፎችም ሁሉ ወይኑን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 13 ወይኑም፦ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጅነቴን ትቼ በዛፎች ላይ እነግሥ ዘንድ ልሂድን? አላቸው። 14 ዛፎችም ዶግን፦ መጥተሽ በላያችን ንገሺ አሉአት፤ 15 ዶግም ዛፎቹን፦ በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ካነገሣችሁኝ እሳት ከዶግ ወጥቶ የሊባኖስን ዝግባ ካልበላው ከጥላዬ በታች ታርፉ ዘንድ ኑ አለቻቸው። 16 አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም፥ ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደሆነና እንደ እጁም ዋጋ መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ 17 አባቴስ ለእናንተ እንደ ተጋደለ፥ በፊታችሁም ሰውነቱን ለሞት አሳልፎ እንደ ሰጠ፥ ከምድያምም እጅ እንደ አዳናችሁ፥ 18 እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋል፤ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ገድላችኋል፤ ወንድማችሁም ስለሆነ የዕቅብቱን ልጅ አቤሜሌክን በሰቂማ ሰዎች ላይ አንግሣችኋል፥ 19 ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ የተባረካችሁ ሁኑ፤ በአቤሜሌክም ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤ 20 እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ትውጣ፤ የሰቂማንም ሰዎች፥ የመሐሎንንም ቤት ትብላ፤ ያም ባይሆን ከሰቂማ ሰዎች ከመሐሎንም ቤት እሳት ትውጣ፤ አቤሜሌክንም ትብላው።” 21 ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፤ ወንድሙን አቤሜሌክንም ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። የአቤሜሌክ መውደቅ 22 አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ገዥ ሆነ። 23 እግዚአብሔርም በአቤሜሌክና በሰቂማ ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሰቂማም ሰዎች የአቤሜሌክን ቤት ከዱት። 24 ይህም የሆነው፥ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ የተደረገው ዐመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሰቂማ ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው። 25 የሰቂማም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፤ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፤ ለአቤሜሌክም ይህን አወሩለት። 26 የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጣ፤ የሰቂማ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ። 27 ወደ እርሻውም ወጡ፤ ወይናቸውንም ለቀሙ፤ ጠመቁትም፤ የደስታም በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፤ በሉም፤ ጠጡም፤ አቤሜሌክንም ረገሙት። 28 የአቤድም ልጅ ገዓል፥ “አቤሜሌክ ማን ነው? እንገዛለትስ ዘንድ የሴኬም ልጅ ማን ነው? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ጠባቂ አይደለምን? ከሴኬም አባት ከኤሞር ሰዎች ጋርስ አገልጋዩ አይደለምን? ስለምንስ ለዚህ እንገዛለን? 29 ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር” አለ። አቤሜሌክንም፥ “ሠራዊትህን አብዝተህ ና፤ ውጣ” አለው። 30 የከተማዪቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 31 እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ ከእጅ መንሻ ጋር መልእክተኞችን ላከ፥ “እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሰቂማ መጥተዋል፤ እነሆም፥ በአንተ ምክንያት ከተማዪቱን ይወጓታል። 32 አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፤ በሜዳም ሸምቁ፤ 33 ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፤ ከተማዪቱንም ክበባት፤ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት።” 34 አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሌሊት መጡ። ሰቂማንም በአራት ወገን ከበቡአት። 35 በነጋም ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማዪቱ መግቢያ በር ቆመ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብም ከሸመቁበት ስፍራ ተነሡ። 36 የአቤድ ልጅ ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን፥ “እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል” አለው። ዜቡልም፥ “ሰዎችን የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ” አለው። 37 ገዓልም ደግሞ፥ “እነሆ፥ ሕዝብ በባሕር በኩል ወደ ምድር መካከል ይወርዳል፤ የአንድም አለቃ ሠራዊት በአድባሩ ዛፍ መንገድ አንጻር ይመጣል” ብሎ ተናገረ። 38 ዜቡልም፥ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ” አለው። 39 ገዓልም በሰቂማ ሰዎች ፊት ወጣ፤ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ። 40 አቤሜሌክም አሳደደው፤ በፊቱም ሸሸ፤ እስከ ከተማው በርም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ። 41 አቤሜሌክም በአሪማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሰቂማ እንዳይኖሩ ከለከላቸው። 42 በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፤ ለአቤሜሌክም ነገሩት። 43 ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፤ በሜዳም ሸመቀ፤ ተመለከተም፤ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፤ ተነሣባቸውም፤ ገደላቸውም። 44 አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ሠራዊት በከተማዪቱ መግቢያ በር ሸምቀው ቆሙ። እነዚያ ሁለቱ ሠራዊት ግን ወደ ጫካው ተበትነው አጠፉአቸው። 45 አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማዪቱ ጋር ተዋጋ፤ ከተማዪቱንም ይዞ በእርስዋ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፤ ከተማዪቱንም አፈረሰ፤ ጨውም ዘራባት። 46 በሰቂማም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ በዓል ቤት ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ። 47 ለአቤሜሌክም በሰቂማ ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ነገሩት። 48 አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሄርሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ አንሥቶም በጫንቃው ላይ ተሸከመው፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ፥ “እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ” አላቸው። 49 ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፤ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፤ ምሽጉንም በላያቸው በእሳት አቃጠሉት፤ የሰቂማም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ። 50 አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ መጣ። 51 በእርስዋም ተቀመጠ፤ እጅም አደረጋት። በከተማዪቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፤ የከተማዪቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፤ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ። 52 አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ሄደ። እነርሱም ተዋጉት። አቤሜሌክም በእሳት ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ቀረበ። 53 አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፤ አናቱንም ሰበረችው። 54 እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ፥ “ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው፤ ጐልማሳውም ወጋው፤ አቤሜሌክም ሞተ። 55 የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ። 56 እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ቤት ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት። 57 እግዚአብሔርም የሰቂማን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፤ የይሩበኣል ልጅ የኢዮአታምም ርግማን ደረሰባቸው። |