መሳፍንት 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጌዴዎን የመጨረሻው ድል 1 የኤፍሬም ሰዎችም፥ “ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም?” አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት። 2 እርሱም፥ “እኔ ዛሬ እናንተ እንዳደረጋችሁት ምን አደረግሁ? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዜር ወይን መከር አይሻልምን? 3 እግዚአብሔር የምድያምን አለቆች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖርአል?” አላቸው። ከዚህ በኋላ ተዉት፤ ይህን ቃል በተናገራቸውም ጊዜ መንፈሳቸው ዐረፈች። 4 ጌዴዎንም ወደ ዮርዳኖስ መጥቶ ተሻገረ፤ ከእርሱም ጋር ያሉት ሦስት መቶ ሰዎች ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ቢራቡም ያሳድዱ ነበር። 5 የሱኮትንም ሰዎች፥ “ተርበዋልና እኔን ለተከተሉ ሰዎች እባካችሁ እህል ስጡአቸው፤ እኔም የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን አሳድዳለሁ” አላቸው። 6 የሱኮትም አለቆች፥ “እኛ ለሠራዊትህ እህል እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን?” አሉ። 7 ጌዴዎንም፥ “እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ቢሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኩርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ” አለ። 8 ከዚያም ወደ ፋኑሄል ወጣ፤ ለፋኑሄልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የፋኑሄልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት። 9 እርሱም የፋኑሄልን ሰዎች፥ “በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” ብሎ ተናገራቸው። 10 ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሃያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ ዐሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። 11 ጌዴዎንም በድንኳን የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት መንገድ በኖቤትና በዮግቤል በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ሳለ አጠፋቸው። 12 ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፤ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፤ ጌዴዎንም ሠራዊቱን ሁሉ አጠፋ። 13 የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎንም ከአሬስ ዳገት ከጦርነት ተመለሰ። 14 ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ መረመረው፤ እርሱም ሰባ ሰባቱን የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎችን አስቈጠራቸው። 15 ጌዴዎንም ወደ ሱኮት አለቆች መጥቶ፥ “ለደከሙት ሰዎችህ እህል እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥” አለ። 16 የከተማዪቱንም ሽማግሌዎችና አለቆች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኩርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው። 17 የፋኑሄልንም ግንብ አፈረሰ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ገደላቸው። 18 ዛብሄልንና ስልማናን፥ “በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “እንዳንተ ያሉ ነበሩ፤ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ነገሥት ልጆች መልክ ነበረ” ብለው መለሱለት። 19 ጌዴዎንም፥ “የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር” አለ። 20 በኵሩንም ዮቶርን፥ “ተነሥተህ ግደላቸው” አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ትንሽ ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21 ዛብሄልና ስልማናም፥ “ኀይልህ እንደ ጐልማሳ ኀይል ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን” አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፤ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ። 22 የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን፥ “ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ፥ ልጅህም፥ የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን” አሉት። 23 ጌዴዎንም፥ “እኔ አልገዛችሁም፤ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል እንጂ” አላቸው። 24 እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን፥ “ሁላችሁም ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ” አላቸው። 25 እነርሱም፥ “መስጠትን ፈቅደን እንሰጥሃለን” ብለው መለሱለት። መጐናጸፊያም አነጠፉ፤ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ። 26 የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ። 27 ጌዴዎንም ምስል አድርጎ ሠራው፤ በከተማውም በኤፍራታ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎ አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። 28 ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፤ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች። የጌዴዎን ሞት 29 የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። 30 ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከአብራኩ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። 31 በሴኬምም የነበረችው ዕቅብቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። 32 የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ በአብያዜራውያንም ከተማ በኤፍራታ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። 33 እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፤ በዓሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በዓሊምም አምላክ ይሆናቸው ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገቡ። 34 የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤ 35 እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ይሩበኣል ለተባለው ለጌዴዎን ቤት ወረታ አላደረጉም። |