መሳፍንት 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል እንደ አደረገ 1 ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፤ በአሮኤድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ። 2 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፤ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም።” 3 እግዚአብሔርም አሁን እንግዲህ፥ “የፈራ፥ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ” አለው። ከሕዝቡም ሃያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፤ ዐሥርም ሺህ ቀሩ። 4 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፤ ወደ ውኃ አውርዳቸው፤ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፤ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም” አለው። 5 ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፤ እንዲሁም ሊጠጣ በጕልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው” አለው። 6 በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቍጥር ሦስት መቶ ሆነ፤ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጕልበታቸው ተንበረከኩ። 7 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያምንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ” አለው። 8 የሕዝቡንም ስንቅና ቀንደ መለከት በእጃቸው ወሰዱ፤ የቀሩትንም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፤ ሦስቱን መቶ ሰዎች ግን በእርሱ ዘንድ ጠበቃቸው፤ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ። 9 በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር፥ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና ተነሥተህ ወደ ሰፈር ውረድ። 10 ብቻህንም ለመውረድ ብትፈራ አንተ ከሎሌህ ፋራን ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ 11 የሚናገሩትንም አድምጣቸው፤ ከዚያም በኋላ እጆችህ ይበረታሉ፤ ወደ ሰፈርም ትወርዳለህ” አለው። እርሱም ከሎሌው ፋራን ጋር ከሰፈሩ በአንድ ወገን የአምሳ አለቃ ጦር ወደ ሰፈረበት ወረደ። 12 ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ልጆች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት ቍጥር እንደሌለው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ። 13 ጌዴዎንም በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለባልንጀራው ሲያጫውት፥ “እነሆ፥ ሕልም አለምሁ፤ እነሆም፥ አንዲት የገብስ እንጎቻ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ወረደች፤ ወደ ድንኳኑም ደርሳ እስኪወድቅ ድረስ መታችው፤ ገለበጠችውም፤ ድንኳኑም ወደቀ” ይል ነበር። 14 ባልንጀራውም መልሶ፥ “ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፤ እግዚአብሔር ምድያምንና ሠራዊቱን ሁሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል” አለው። 15 ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜዉን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ፥ “እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ” አለ። 16 ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፤ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮዉም ውስጥ ችቦ ሰጣቸው። 17 እርሱም፥ “እኔን ተመልከቱ፤ እንዲሁም አድርጉ፤ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፤ 18 እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ፦ ኀይል የእግዚአብሔር፥ ሰይፍ የጌዴዎን በሉ” አላቸው። 19 ጌዴዎንም፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት መጀመሪያ ዘብ ጠባቂዎች ሳይነቁ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፤ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮዎች ሰባበሩ፤ 20 ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፤ ማሰሮዎችንም ሰበሩ፤ በግራ እጃቸውም ችቦዎችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ፥ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” ብለው ጮኹ። 21 ሁሉም በየቦታው፥ በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ደንግጠው ሸሹ። 22 ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶችን ነፉ፤ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራዉና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፤ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሲጣ ጋራጋታ ድረስ በጣባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልሜሁላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። 23 የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር፥ ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ። 24 ጌዴዎንም፥ “ምድያማውያንን ለመግጠም ውረዱ፥ እስከ ቤትባራም ድረስ ያለውን ውኃ፥ ዮርዳኖስንም፥ ያዙባቸው” ብሎ መልእክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ተራራማ ሀገር ሁሉ ላከ። የኤፍሬምም ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው እስከ ቤትባራ ድረስ ውኃውን፥ ዮርዳኖስንም ቀድመው ያዙ። 25 የምድያምን ሁለቱን አለቆች ሔሬብንና ዜብን ያዙ፤ ሔሬብንም በሱርኤራብ ገደሉት፥ ዜብንም በኢያፌቅ ገደሉት፤ የምድያምንም ሰዎች አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ጌዴዎን አመጡ። |