መሳፍንት 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ስለ በደሉ በምድያማውያን እጅ እንደ ወደቁ 1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። 2 የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም ፊት የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራሮችና በገደሎች ላይ ጕድጓድና ዋሻ፥ ምሽግም አበጁ። 3 የእስራኤልም ልጆች ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያንና አማሌቃውያን ይዘምቱባቸው ነበር፥ በምሥራቅም የሚኖሩ ልጆች አብረው ይዘምቱባቸው ነበር፤ 4 በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፤ ወደ ጋዛም እስከሚደርሱ የእርሻቸውን ፍሬ ያጠፉ ነበር፤ በእስራኤልም ምድር ለሕይወት የሚሆን ምንም አይተዉም ነበር፤ ከመንጋዎችም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም ነበር። 5 እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡባቸው ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸው ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፏት ዘንድ ይመጡ ነበር። 6 ከምድያምም ፊት የተነሣ እስራኤል እጅግ ተቸገሩ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔር ጌዴዎንን ለእስራኤል እንደ አስነሣላቸው 7 እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ 8 እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፤ እርሱም አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤ 9 ከግብፃውያንም እጅ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፤ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፤ ሀገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤ 10 እናንተንም፦ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።” 11 የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በኤፍራታ ባለችው ለኤዝሪ አባት ለኢዮአስ በነበረችው ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለማሸሽ በወይን መጭመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። 12 የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፥ “አንተ ጽኑዕ ኀያል ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። 13 ጌዴዎንም፥ “ጌታዬ ሆይ! እሺ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራት ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያም እጅም አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። 14 የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ እርሱ ተመለከተና፥ “በዚህ በጕልበትህ ሂድ፤ እስራኤልንም ከምድያም እጅ ታድናቸዋለህ፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ” አለው። 15 እርሱም፥ “ጌታ ሆይ! እሺ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ በምናሴ ነገድ ዘንድ ጥቂቶች ናቸው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” አለው። 16 የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ታጠፋለህ” አለው። 17 ጌዴዎንም፥ “በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አድርግልኝ፤ 18 ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትሂድ” አለው። እርሱም፥ “እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው። 19 ጌዴዎንም ሄደ፤ የፍየሉንም ጠቦት፥ የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውንም በሌማት አኖረ፤ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፤ ሁሉንም ይዞ በዛፍ በታች አቀረበለት። ሰገደለትም። 20 የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፤ መረቁንም አፍስስ” አለው። እንዲሁም አደረገ። 21 የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን በትሩን ዘርግቶ ሥጋዉንና የቂጣዉን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥታ ሥጋዉንና የቂጣዉን እንጎቻ በላች። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዐይኖቹ ተሰወረ። 22 ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ ዐወቀ። ጌዴዎንም፥ “አቤቱ! አምላኬ ሆይ! ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና” አለ። 23 እግዚአብሔርም፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። 24 ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም እስከ ዛሬ ድረስ “የእግዚአብሔር ሰላም” ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለኤዝሪ አባት በሆነችው በኤፍራታ አለ። 25 እንዲህም ሆነ፤ በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር፥ “የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ ውሰድ፤ የአባትህ የሆነውንም የበዓል መሠዊያ አፍርስ፤ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐጸድ ቍረጥ፤ 26 በዚያም ተራራ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ፤ ሁለተኛዉንም በሬ ውሰድ፤ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐጸዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። 27 ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ ዐሥራ ሦስት ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱንም ቤተ ሰቦች፥ የከተማዉንም ሰዎች ስለፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፤ ነገር ግን በሌሊት አደረገው። 28 የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፤ እነሆም፥ የበዓል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያውም ያለው የማምለኪያ ዐጸድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት። 29 እርስ በርሳቸውም፥ “ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው?” ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ፥ “ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው” አሉ። 30 የከተማዉም ሰዎች ኢዮአስን፥ “የበዓልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐጸድ ቈርጦአልና ይገደል ዘንድ ልጅህን አምጣ” አሉት። 31 ኢዮአስም በእርሱ ላይ የተነሡበትን ሁሉ፥ “ለበዓል እናንተ ዛሬ ትበቀሉለታላችሁን? ወይስ የበደለውን ትገድሉለት ዘንድ የምታድኑት እናንተ ናችሁን? እርሱ አምላክ ከሆነስ የበደለው እስከ ነገ ድረስ ይሙት። መሠዊያዉንም ያፈረሰውን እርሱ ይበቀለው” አላቸው። 32 በዚያች ቀንም መሠዊያዉን አፍርሶአልና በዓል ከእርሱ ጋር ይሟገት ሲል ጌዴዎንን ይሩበኣል ብሎ ጠራው። 33 ምድያምና አማሌቅም ሁሉ፥ የምሥራቅም ልጆች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፤ ተሻግረውም በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ። 34 ጌዴዎንንም የእግዚአብሔር መንፈስ አጸናው፤ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ አብዔዜርም በኋላው ጮኸ። 35 ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልእክተኞችን ላከ፤ እርሱም ከኋላው ሆኖ ጮኸ፤ መልእክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ላከ፤ እነርሱም ሊቀበሉአቸው ወጡ። 36 ጌዴዎንም እግዚአብሔርን፥ “እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥ 37 እነሆ! በዐውድማዉ ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንደምታድናቸው አውቃለሁ” አለ። 38 እንዲሁም ሆነ፤ በነጋው ማልዶ ተነሣ፤ ጠጕሩንም ጨመቀው፤ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል አንድ መንቀል ሙሉ ውኃ ሆነ። 39 ጌዴዎንም እግዚአብሔርን አለው፥ “በቍጣህ አትቈጣኝ፤ ደግሞ አንዲት ነገር ልናገር፤ ጠጕሩ ብቻውን ደረቅ ይሁን፤ በምድሩም ላይ ጠል ይውረድ።” 40 እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ ጠጕሩ ብቻ ደረቅ ሆነ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ወረደ። |