መሳፍንት 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዲቦራና የባርቅ መዝሙር 1 በዚያችም ቀን ዲቦራና የአቢኒሔም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ዘመሩ፦ 2 በእስራኤል ውስጥ መሳፍንት ስለ መሩ ሕዝቡም ስለ ፈቀዱ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 3 ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ ጽኑዓን መኳንንትም ሆይ፥ አድምጡ፤ እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤ እኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። 4 አቤቱ! ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፤ ሰማያትም ጠልን አንጠባጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠባጠቡ። 5 ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ተነዋወጡ፤ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ፤ 6 በሐናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን ነገሥት መንገዶችን ተዉ፤ በስርጥ መንገድም ይሄዱ ነበር፤ በጠማማ መንገድም ሄዱ። 7 መተርጕማን ከእስራኤል ዘንድ አለቁ፥ ዲቦራ እስክትነሣ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆና እስክትነሣ ድረስ አለቁ። 8 አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታዩም። 9 ልቤ ለእስራኤል ወደ ታዘዘው ትእዛዝ ነው፤ እናንተ የእስራኤል ኀያላን፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 10 በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በፍርድ ወንበር ላይየምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ በቃላችሁ ተናገሩ። 11 በብዙዎች ደስተኞች መካከል መሰንቆን ምቱ፤ በዚያ ለእግዚአብሔር የጽድቅ ሥራን፥ በእስራኤልም ውስጥ ጽድቅንና ኀይልን ያቀርባሉ። ያንጊዜም የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ከተማዎቹ ወረዱ። 12 ተነሺ፥ ዲቦራ ሆይ፦ ተነሺ፤ አእላፍን ከሕዝብ ጋር አስነሺ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ቅኔውንም ተቀኚ፤ ባርቅ ሆይ! በኀይል ተነሣ፤ ዲቦራም ባርቅን አጽኚው፥ የአቢኒሔም ልጅ ባርቅም ሆይ! ምርኮህን ማርክ። 13 በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኀያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤ እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኀያላን ላይ ወረደ። 14 በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ! በሕዝብ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ። 15 የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኮሉ፤ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ። 16 መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት፥ በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ። 17 ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ። 18 ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፤ ንፍታሌምም በሀገሩ ኮረብታ ላይ ነው። 19 ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጌዶ ውኆች አጠገብ በቶናሕ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ በቅሚያም ብርን አልወሰዱም። 20 ከዋክብት በሰማይ ተዋጉ፤ በሰልፋቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። 21 ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በርቺ። 22 ያን ጊዜ ከኀያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ፥ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። 23 የእግዚአብሔር መልአክ አለ፥ “ሜሮዝን ርገሙ፤ ወደ እግዚአብሔር ርዳታ አልመጡምና፥ በኀያላን መካከል ወደ እርሱ ርዳታ አልመጡምና፥ በቤቶችዋ ያሉትን ሰዎች ፈጽማችሁ ርገሙ።” 24 የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል፥ ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። 25 ውኃ ለመነ፤ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። 26 ግራ እጅዋን ወደ ካስማ፤ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታችው፤ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮ ግንዱንም በሳች፤ ጐዳችውም። 27 በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፤ ወደቀ፤ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተፈራገጠ፤ በተፈራገጠበትም በዚያ ተጐሳቍሎ ሞተ። 28 የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ በሰቅሰቅም ዘልቃ፦ ከሲሣራ የተመለሰ እንዳለ አየች፤ ስለምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። 29 ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ 30 ምርኮውን ሲካፈል፥ በኀያላኑም ቸብቸቦ ላይ ወዳጆችን ሲወዳጅ ያገኙት አይደለምን? የሲሣራ ምርኮ በየኅብሩ ነበረ፤ የኅብሩም ቀለም የተለያየ ነበረ፤ የማረከውም ወርቀ ዘቦ ግምጃ በአንገቱ ላይ ነበረ። 31 አቤቱ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኀይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፤ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች። |