መሳፍንት 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር መልአክ በቀላውትምኖስ 1 የእግዚአብሔርም መልአክ ከገልገላ ወደ ቀላውትምኖስ ወደ ቤቴል ወደ እስራኤል ቤት ወጥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እኔ ከግብፅ አውጥቼአችኋለሁ፤ እሰጣችሁም ዘንድ ለአባቶቻችሁ ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም፦ ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘለዓለም አላፈርስም፤ 2 እናንተም በዚች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ ለአማልክቶቻቸውም አትስገዱላቸው፤ ምስሎቻቸውንም ስበሩ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? 3 ስለዚህም እኔ አሕዛብን ከፊታችሁ አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፤ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል” አልሁ። 4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። 5 የዚያም ስፍራ ስም “መካነ ብካይ” ተብሎ ተጠራ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ። የኢያሱ ሞት 6 ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደየርስታቸው ገቡ። 7 ኢያሱም በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ ለእስራኤልም ያደረገውን ታላቁን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት፥ ከኢያሱ በኋላ በነበሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ተገዙ። 8 የእግዚአብሔርም አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። 9 በተራራማዉ በኤፍሬም ሀገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። 10 ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተጨመሩ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርንና ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ። እስራኤል አምልኮተ እግዚአብሔርን መተዋቸው 11 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረጉ፤ በዓሊምንም አመለኩ። 12 ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ ሌሎችንም በዙሪያቸው ያሉ የአሕዛብን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡት። 13 እግዚአብሔርንም ትተው በዓልንና አስታሮትን አመለኩ። 14 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ተቈጣ፤ ወደ ማረኳቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ማረኩአቸውም፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ከዚያም ወዲያ ጠላቶቻቸውን ሊቋቋሙ አልቻሉም። 15 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደ ማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ። እግዚአብሔር ለእስራኤል መሳፍንትን እንደ አስነሣላቸው 16 እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፤ ከሚማርኳቸውም እጅ አዳኗቸው። 17 ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ፥ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ የእግዚአብሔርንም ቃል እንዳይሰሙ አባቶቻቸው ይሄዱባት የነበረችውን መንገድ ፈጥነው ተዉአት፤ እንዲሁም አላደረጉም። 18 እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም በሚዋጉአቸው ሰዎች ፊት ከመከራቸው የተነሣ ይቅር ብሏቸዋልና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው። 19 መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ዳግመኛ ተመልሰው ከአባቶቻቸው ይልቅ እጅግ ይበድሉ፤ ነበር፤ ሂደውም ሌሎች አማልክትን ተከትለው ያመልኳቸው ነበር፤ ይሰግዱላቸውም ነበር፤ ክፋታቸውንም አይተዉም ነበር፤ ከክፉ መንገዳቸውም አይመለሱም ነበር። 20 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ቃሌንም ስላልሰሙ፥ 21 እኔም የነዌ ልጅ ኢያሱ ትቶአቸው ከአለፈ አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳን ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም። 22 አባቶቻቸው እንደ ጠበቁ፥ ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፤” 23 እግዚአብሔርም እነዚህን አሕዛብ አስቀረ፤ ፈጥኖም አላወጣቸውም፤ በኢያሱም እጅ አሳልፎ አልሰጣቸውም። |