መሳፍንት 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሚካና የዳን ነገድ 1 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የዳን ነገድ የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር። 2 የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ፥ “ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ” ብለው ከሶራሕና ከኢስታሔል ላኩ። እነዚያም ወደ ተራራማዉ ወደ ኤፍሬም ሀገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። 3 በሚካ ቤትም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊዉን የጐልማሳውን ድምፅ ዐወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው፥ “ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድን ነው? በዚህስ ምን አለህ?” አሉት። 4 እርሱም፥ “ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፤ ቀጠረኝም፤ እኔም ካህን ሆንሁለት” አላቸው። 5 እነርሱም፥ “የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት። 6 ያም ካህን፥ “የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በሰላም ሂዱ” አላቸው። 7 አምስቱም ሰዎች ሄዱ፤ ወደ ሌሳም ደረሱ፤ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፤ እንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው፥ ዐርፈው፥ ተዘልለውም ተቀምጠው ነበር፤ በተመዘገበች የርስታቸው ምድርም ቃልን መናገር አልቻሉም፤ ከሲዶናውያንም ርቀው ይኖሩ ነበር። ከሶርያውያንም ጋር ግንኙነት አልነበራቸውም። 8 እነዚያም አምስቱ ሰዎች ወደ ወንድሞቻቸው ወደ ሶራሕና ወደ እስታሔል ተመለሱ፤ ወንድሞቻቸውንም፥ “ምን አስቀምጦአችኋል?” አሉአቸው። 9 እነርሱም፥ “ምድሪቱ እጅግ መልካም እንደ ሆነች አይተናል፤ ተነሡ፤ በእነርሱ ላይ እንውጣ፤ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ፥ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ። 10 በሄዳችሁም ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፤ ምድሪቱም ሰፊ ናት፤ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጐድልባትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል” አሉ። 11 ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከሶራሕና ከእስታሔል ተነሥተው ሄዱ። 12 ወጥተውም በይሁዳ ቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፤ እነሆም፥ ቦታዉ ከቂርያትይዓሪም በስተኋላ ነው። 13 ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ እስከ ሚካም ቤት ደረሱ። 14 የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን፥ “በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኢፉድና ተራፊም፥ የተቀረፀ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን?፤ አሁንም የምታደርጉትን ዕወቁ” ብለው ተናገሩአቸው። 15 ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ወደ ጐልማሳው ሌዋዊ ቤት ወደ ሚካ ቤት መጡ፤ ሰላምታም ሰጡት። 16 የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስቱ መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር። 17 ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች መጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረፀውንም ምስል ኤፉዱንም፥ ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር። 18 እነዚህም ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረፀውን ምስል፥ ኤፉዱንም፥ ተራፊሙንም፥ ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም፥ “ምን ታደርጋላችሁ?” አላቸው። 19 እነርሱም፥ “ዝም በል፤ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፤ ከእኛም ጋር ና፥ አባትና ካህንም ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል?” አሉት። 20 ካህኑም በልቡ ደስ አለው፤ ኤፉዱንም፥ ተራፊሙንም፥ የተቀረፀውንም ምስል፥ ቀልጦ የተሠራውንም ምስል ወሰደ፤ በሕዝቡም መካከል ገባ። 21 እነርሱም ተመልሰው ሄዱ፤ ቤተ ሰቡን፥ ገንዘቡንና ሀብቱንም ሁሉ፥ በፊታቸው አድርገው ወሰዱ። 22 ከሚካም ቤት ሳይርቁ ሚካና የሚካ ጎረቤቶች ጮኹ፤ የዳንንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው። የዳን ሰዎች በሌሳ እንደ ሰፈሩ 23 ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፤ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን፥ “የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው?” አሉት። 24 እርሱም፥ “የሠራኋቸውን አማልክቴን፥ ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፤ ለእኔ ምን ተዋችሁልኝ? እናንተስ፦ ለምን ትጮኻለህ እንዴት ትሉኛላችሁ?” አለ። 25 የዳንም ልጆች እንዲህ አሉት፥ “የተቈጡ ሰዎች እንዳያገኙህና ነፍስህም፥ የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህ በእኛ መካከል አይሰማ።” 26 የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።። 27 እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ መጡ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሉአት። 28 የሚታደግም አልነበረም፤ ከሲዶና ርቀው ነበርና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት አልነበራቸውምና። እርስዋም በቤትሮአብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች፤ ከተማዪቱንም ሠርተው ተቀመጡባት። 29 ከተማዪቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ የከተማዪቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ። 30 የዳንም ልጆች የተቀረፀውን የሚካን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ እስከ ሀገራቸው ምርኮ ድረስ ለዳን ነገድ ካህናት ነበሩ። 31 ሚካም ያደረገውን የተቀረፀ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ። |