መሳፍንት 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮፍታሔና የኤፍሬም ሰዎች 1 የኤፍሬምም ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን፥ “ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን” አሉት። 2 ዮፍታሔም፥ “እኔና ሕዝቤ የተገፋን ነን፤ የአሞን ልጆችም በጽኑዕ አሠቃዩን፤ በጠራናችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁንም። 3 የሚያድን እንደሌለም ባየሁ ጊዜ ሰውነቴን በእጄ አሳልፌ ለሞት በመስጠት ወደ አሞን ልጆች ተሻገርሁ፤ እግዚአብሔርም በፊቴ ጣላቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ?” አላቸው። 4 ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም፥ “ገለዓዳውያን ሆይ! እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁ ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው” ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ። 5 የገለዓድ ሰዎችም ኤፍሬም በሚያልፍበት በዮርዳኖስ ማዶ ደረሱባቸው። ከዚህ በኋላ ከኤፍሬም ያመለጡት እንሻገር ባሉ ጊዜ የገለዓድ ሰዎች፥ “በውኑ እናንተ ከኤፍሬም ወገን ናችሁን?” ቢሉአቸው “አይደለንም” አሉ። 6 እነርሱም፥ “አሁን ሺቦሌት በሉ” አሉአቸው፤ እነርሱም አጥርተው መናገር አልቻሉምና፥ “ሲቦሌት” አሉ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሸጋገርያ አረዱአቸው፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ። 7 ዮፍታሔም እስራኤልን ስድስት ዓመት ገዛ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔም ሞተ፤ በሀገሩ በገለዓድም ተቀበረ። 8 ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ሐሴቦን እስራኤልን ገዛ። 9 ሠላሳ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ ሀገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ ሀገር ሠላሳ ሴቶች ልጆችን አመጣ። እስራኤልንም ሰባት ዓመት ገዛ። 10 ሐሴቦንም ሞተ፤ በቤተ ልሔምም ተቀበረ። 11 ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎን እስራኤልን ዐሥር ዓመት ገዛ። 12 ዛብሎናዊው ኤሎንም ሞተ፤ በዛብሎንም ምድር በኤሎም ተቀበረ። 13 ከእርሱም በኋላ የኤፍራታዊው የኤሎን ልጅ ለቦን እስራኤልን ገዛ። 14 አርባም ልጆች፥ ሠላሳም የልጅ ልጆች ተወለዱለት፤ በሰባም የአህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። እስራኤልንም ስምንት ዓመት ገዛ። 15 የኤፍራታዊው የኤሎን ልጅ ለቦንም ሞተ፤ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በኤፍራታ ተቀበረ። |