መሳፍንት 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳና የስምዖን ነገድ አዶኒቤዜቅን እንደ ማረኩ 1 እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች፥ “ከነዓናውያንን የሚወጋልን ማን አለቃ ይወጣልናል?” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጠየቁ። 2 እግዚአብሔርም፥ “ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቼአታለሁ” አለ። 3 ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን፥ “ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፤ ከነዓናውያንንም እንውጋቸው፤ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ” አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ። 4 ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዜዎናውያንን በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ ዐሥር ሺህ ሰዎችን ገደለባቸው። 5 አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዜዎናውያንንም ገደሉአቸው። 6 አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ ተከታትለውም ያዙት፤ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣቶች ቈረጡ። 7 አዶኒቤዜቅም፥ “የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበሩ፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ” አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ወሰዱት፥ በዚያም ሞተ። ኢየሩሳሌምና ኬብሮን በይሁዳ ነገድ እንደ ተያዙ 8 የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፤ በሰይፍ ስለትም መቱአት፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሉአት። 9 ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው ሀገርና በደቡብ በኩል በቈላው ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ። 10 ይሁዳም በኬብሮን ወደሚኖሩ ከነዓናውያን ሄደ። የኬብሮንም ሰዎች ወጥተው ተቀበሉት፤ የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያታርቦቅሴፌር ነበረ። የኤናቅንም ትውልድ ሴሲንና አኪማምን፥ ተለሜንንም ገደሉአቸው። ጎቶንያል ዳቤርን መያዙ ( ኢያ. 15፥13-19 ) 11 ከዚያም ወደ ዳቤር ሰዎች ሄዱ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ሀገረ መጻሕፍት ነበረ። 12 ካሌብም፥ “ሀገረ መጻሕፍትን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓስካን ሚስት ትሆነው ዘንድ እሰጠዋለሁ” አለ። 13 የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ሚስትም ትሆነው ዘንድ ልጁን ዓስካን ሰጠው። 14 እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ የእርሻ ቦታ ይሰጣት ዘንድ አባቷን እንድትለምነው ጎቶንያል መከራት። እርስዋም በአህያዋ ላይ ሆና አንጐራጐረች፤ “ወደ ደቡብ ሰድደኸኛል” ብላም ጮኸች። ካሌብም፥ “ምን ሆነሻል?” አላት። 15 ዓስካም፥ “በረከትን ስጠኝ፤ ወደ ደቡብ በረሃ ሰድደኸኛልና ውኃ የማጣቴን ዋጋ ደግሞ ስጠኝ” አለችው። ካሌብም በልብዋ እንደ ተመኘችው የመከራዋንና የኀዘኗን ዋጋ ሰጣት። የይሁዳና የብንያም ነገድ ድል እንደ ተቀዳጁ 16 የቄናዊው የሙሴ አማት የዮባብ ልጆችም ከዘንባባ ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በአዜብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወደ ይሁዳ ልጆች ሄደው ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ። 17 ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፤ በሴፌት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፤ ፈጽመውም አጠፉአት፤ የከተማዪቱንም ስም ሕርም ብለው ጠሩአት። 18 ይሁዳም ጋዛንና አውራጃዋን፥ አስቀሎናንና አውራጃዋን፥ አቃሮንንና አውራጃዋን፥ አዛጦንንና አውራጃዋን አልወረሳትም። 19 እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን ሀገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩትን ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊወርሳቸው አልቻለም። 20 ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሠላሳ ከተሞችን ወረሰ፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አስወገዳቸው። 21 ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሴዎናውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሴዎናውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል። ቤቴል በኤፍሬምና በምናሴ መያዝዋ 22 የዮሴፍም ልጆች ደግሞ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ። 23 እነርሱም ሰፍረው ቤቴልን ሰለሉአት። አስቀድሞም የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ይባል ነበር። 24 ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው ያዙትና፥ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት። 25 የከተማዪቱንም መግቢያ አሳያቸው፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት መቱአት፤ ያን ሰውና ዘመዶቹን ግን ለቀቁአቸው። 26 ሰውየውም ወደ ኬጤዎናውያን ምድር ሄደ፤ በዚያም ከተማን ሠራ፤ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ያው ነው። እስራኤላውያን ያላባረሩት ሕዝብ 27 ምናሴም የሰቂቶን ከተማ ቤትሶንንና መንደሮችዋን መሰማሪያዎችዋንም፥ ኢቀጸአድንና መንደሮችዋን፥ የዶርን ነዋሪዎችና መንደሮችዋን፥ የዮበለዓምን ነዋሪዎች፥ መሰማሪያዎችዋንና መንደሮችዋን፥ የመጊዶን ነዋሪዎች መሰማሪያዎችዋንና መንደሮችዋን አልወረሳቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያች ሀገር ይቀመጡ ዘንድ ጸኑ። 28 እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን ገባሮች አደረጉአቸው፤ ነገር ግን ፈጽመው አላጠፏቸውም። 29 ኤፍሬምም በጋዜር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላጠፋቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጋዜር ተቀመጡ፤ ገባሮችም ሆኑላቸው። 30 ዛብሎንም በቄድሮንና በአማን የሚኖሩትን ሰዎች አላጠፋቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፤ ግብርም የሚገብሩላቸው ሆኑ። 31 አሴርም የዓኮ ነዋሪዎችን አላጠፋቸውም፤ ነገር ግን ገባሮች ሆኑላቸው፤ የዶር ነዋሪዎችንና የሲዶን ነዋሪዎችን፥ የደላፍንም ነዋሪዎች፥ የአክሶዚብንና የሄልባን፥ የአፌቅንና የረዓብንም ሰዎች አላጠፉአቸውም። 32 አሴርም በዚያች ምድር በተቀመጡት ከነዓናውያን መካከል ተቀመጠ፤ ሊያጠፋቸው አልቻለምና። 33 ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤቴኔስን ሰዎች አላጠፋቸውም፤ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን በቤትሳሚስና በቤቴኔስ የሚኖሩ ሰዎች ገባሮች ሁኑላቸው። 34 አሞሬዎናውያንም የዳንን ልጆች በተራራማው ሀገር አስጨነቁአቸው፤ ወደ ሸለቆው እንዲወርዱ አይፈቅዱላቸውም ነበርና። 35 አሞሬዎናውያንም ድብና ቀበሮዎች በሚኖሩበት በመርስኖኖስ ተራራ መቀመጥ ጀመሩ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ወገን እጅ በአሞሬዎናውያን ላይ ጸናች፤ ገባርም አደረጉአቸው። 36 የአሞናውያንም ድንበር ከአቅራቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይኛው ድረስ ነበረ። |