ኢዮብ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ጥንቱን በምድር ላይ የሰው ሕይወት ጥላ አይደለምን? ኑሮውስ እንደ ቀን ምንደኛ አይደለምን? 2 ወይም ጌታውን እንደሚፈራ አገልጋይ ጥላውንም እንደሚመኝ፥ ወይም ደመወዙን እንደሚጠብቅ ምንደኛ አይደለምን? 3 እንዲሁ እኔ የከንቱ ወራትን ታገሥሁ፥ የፃዕርም ሌሊት ተወሰነችልኝ። 4 በተኛሁም ጊዜ፦ መቼ ይነጋል? እላለሁ፤ በተነሣሁም ጊዜ ዳግመኛ መቼ ይመሻል? እላለሁ፤ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ መከራን ጠገብሁ። 5 ሥጋዬ በትልና በመግል በስብሶአል፥ ቍስሌን በገል እያከክሁ አለቅሁ። ዐመድም ሆንሁ። 6 ሕይወቴ እንደ ሸማኔ መወርወርያ፥ ቀላል ሆነች በከንቱ ተስፋም ጠፋሁ። 7 ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነች አስብ፤ ዐይኔም መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ አታይም። 8 የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፤ ዐይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፤ እኔም አልገኝም። 9 ደመና ከሰማይ ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ መቃብር የሚወርድ ሰው ዳግመኛ አይወጣም። 10 ወደ ቤቱም ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ እርሱን አያውቀውም። 11 ስለዚህም እኔ አፌን አልከለክልም፤ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፤ የነፍሴንም ምሬት በኀዘን እገልጣለሁ። 12 ጠባቂ አዝዘህብኛልና፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን? 13 እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኝ ይሆን? መኝታዬስ ደስ ያሰኘኝ ይሆን? እላለሁ። 14 አንተም በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤ 15 ሕይወትን ከመንፈሴ ትለያለህ። አጥንቶቼንም ከሞት ትጠብቃለህ። 16 እንድታገሥ ለዘለዓለም እኖራለሁን? ሕይወቴ ከንቱ ነውና ከእኔ ራቅ። 17 ሰው ምንድን ነው? ከፍ ከፍ ታደርገው ዘንድ፥ ልቡናውንም ትጐበኘው ዘንድ፥ 18 ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ በዕረፍቱም ትፈርድለት ዘንድ፥ 19 የማታሳርፈኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? 20 የሰውን ልብ፦ የምታውቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ እንግዲህ ምን ላደርግልህ እችላለሁ? ስለምን እኔን ለመከራ አደረግኸኝ? ስለ ምን በአንተ ላይ እንድናገር በአምሳልህ ፈጠርኸኝ? ስለ ምንስ እኔ ሸክም ሆንሁብህ? 21 ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኀጢአቴንስ ስለ ምን አታነጻም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ በማለዳም አልነቃም።” |