ኢዮብ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮብ መልስ 1 ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “ከእናንተ አንዱ መቅሠፍቴን ምነው በመዘነ ኖሮ! መከራዬንም በአንድነት ምነው በሚዛን ላይ ባኖረው ኖሮ! 3 ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ነገር ግን ቃሌ ሐሰትን ይመስላል። 4 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ፍላጻ በሥጋዬ ላይ ነው፤ መርዙም ደሜን ይመጥጣል። ለመናገር ስጀምርም ይወጋኛል። 5 በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው በከንቱ ይጮኻልን? የሚበላውን ፈልጎ አይደለምን? ወይስ በሬ በበረት ውስጥ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? 6 ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? የጎመን ዘር ጭማቂስ ይጣፍጣልን? ወይስ ለከንቱ ጣዕም አለውን? 7 ሰውነቴ ማረፍ አልቻለችም፤ የሥጋዬን ክርፋት እንደ አንበሳ ክርፋት እመለከተዋለሁና። 8 ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ተስፋዬን ምነው በሰጠኝ! 9 እግዚአብሔርም ያቈስለኝ ዘንድ ጀመረ፥ ነገር ግን እስከ መጨረሻው አላጠፋኝም። 10 መቃብሬ በግንቡ የምመላለስበት ከተማዬ ይሁን፥ ከእርሱም ፈቀቅ አልልም የአምላኬን ቅዱስ ቃል አልካድሁምና። 11 እታገሥ ዘንድ ጕልበቴ ምንድን ነው? ነፍሴም ትጽናና ዘንድ ዘመኔ ምንድን ነው? 12 ጕልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? በውኑ ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? 13 በእርሱ የታመንሁ አይደለሁምን? ረድኤቱ ከእኔ ለምን ራቀ? 14 ምሕረቱ ቸል አለኝ፥ እግዚአብሔር አልጐበኘኝም አልተመለከተኝም። 15 “ወንድሞቼም እንደ ደረቅ ወንዝ፥ እንደ አለፈ ማዕበልም አላወቁኝም። 16 ያከብሩኝ የነበሩ እነዚያ፥ አሁን እንደ በረዶና እንደ ረጋ አመዳይ ሆኑብኝ፤ 17 ወደ ሙቀት ሲቀርብ በቀለጠ ጊዜ ምን እንደ ነበረ አይታወቅም። 18 እንደዚሁም እኔ ከሁሉ ተለይቼ ጠፋሁ፥ ከቤቴም ወጥቼ የተጣልሁ ሆንሁ። 19 የቴማናውያንን መንገዶች፥ የሳባውያንን ክፋትና ቸልተኝነት ተመልከቱ። 20 በከተሞችና በገንዘቦች የሚታመኑ ያፍራሉ። 21 አሁንም እናንተ ያለ ምሕረት መጣችሁ፤ ቍስሌንም አይታችሁ ፈራችሁ። 22 ለምን? በውኑ፦ ከእናንተ አንዳች ነገር ጠየቅሁን? ወይስ፦ ከእናንተ ኀይልን ተመኘሁን? 23 ወይስ ከጠላቶች እጅ ታስጥሉኝ ዘንድ ከኀይለኞችም እጅ ታድኑኝ ዘንድ። 24 “አስተምሩኝ፥ እኔም አዳምጣችኋለሁ፤ የተሳሳትሁትም ካለ አስረዱኝ። 25 የእውነተኛ ሰው ቃል ሐሰትን ይመስላል፥ ከእናንተ ዘንድ ኀይልን የምጠይቅ አይደለምና። 26 የንግግራችሁም ማጽናናት ዕረፍትን አይሰጠኝም፤ የአንደበታችሁም ቅልጥፍና ደስ አያሰኘኝም። 27 በድሃ አደጉ ላይ ትስቃላችሁና፥ ወዳጃችሁንም ትሰድባላችሁና። 28 አሁንም፥ ፊታችሁን አይቼ ሐሰት አልናገርም። 29 አሁንም ተቀመጡ፤ በደልም አይኑር፤ ዳግመኛም ከጻድቁ ጋር አንድ ሁኑ። 30 በአንደበቴ በደል የለምና አፌ ጕሮሮዬም ጥበብን ይናገራል። |