ኢዮብ 41 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አትፈራምን? ለእኔ አዘጋጅተሃልና። የሚቃወመኝስ ማን ነው? 2 የሚከራከረኝና በሕይወት የሚኖርስ ማን ነው? ከሰማይ በታች ያለውም ሁሉ የእኔ ነው። 3 ስለ እርሱ ዝም አልልም፥ የኀይል ቃልም እንደ እርሱ ያለውን ይቅር ይለዋል። 4 የፊቱን መጋረጃ ማን ይገልጣል? ወደ ደረቱ መጋጠሚያ ውስጥስ ማን ይገባል? 5 የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያም ግርማ አለ። 6 አንጀቶቹ የናስ አራዊት ናቸው፤ የቆዳውም ጽናት እንደ ዓለት ድንጋይ ነው። 7 እርስ በርሳቸው የተጣበቁ ናቸውና፥ ነፋስም በመካከላቸው መግባት አይችልም። 8 ሰውን ከወንድሙ ጋር አንድ ያደርጋል፤ እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ ሊለያዩም አይችሉም። 9 እንጥሽታው ብልጭታን ያወጣል፥ ዐይኖቹም እንደ አጥቢያ ኮከብ ናቸው። 10 ከአፉ የሚቃጠል መብራት ይወጣል የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል። 11 የከሰል እሳት እንደሚቃጠልበት ምድጃ ከአፍንጫው ጢስ ይወጣል። 12 እስትንፋሱ እንደ ፍም ናት። ነበልባልም ከአፉ ይወጣል። 13 በአንገቱ ኀይል ታድራለች፤ ለሚያየውም በፊቱ ሞት ይውላል። 14 የአካሉ ሥጋም የተነባበረ ነው፤ ጎጂ ነገርን ቢያፈስሱበትም አይንቀሳቀስም፤ 15 ልቡ እንደ ዋሻ ድንጋይ የደነደነ ነው፤ እንደ ወፍጮ ድንጋይም የጸና ነው። 16 በተመለሰም ጊዜ አራዊትና እንስሳ ይፈራሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ይሸበራሉ። 17 ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት ምንም አያደርጉትም። 18 በእርሱ ዘንድ መውጊያና የብረት ልብስ እንደ ገለባ ናቸው። ናስም እንደ ነቀዘ እንጨት ነው። 19 የናስ ፍላጻ ሊበሳው አይችልም፤ የወንጭፍ ድንጋዮችም በእርሱ ዘንድ እንደ ገለባ ናቸው። 20 ድጅኖ ቀሰም ይመስለዋል በታላላቅ ድንጋዮች ላይ ይሥቃል። 21 መኝታው እንደ ስለታም ድንጋይ ነው፤ የባሕር ወርቅ ሁሉ በእርሱ ዘንድ እንደማይቈጠር ጭቃ ነው። 22 ቀላይዋን እንደ ብረት ድስት ያፈላታል፤ ባሕሩም ምድረ በዳ ይመስለዋል። 23 የሲኦልም ጥልቀት እንደ ምርኮ ነው። ቀላዩንም እንደ መመላለሻ መንገድ ያደርጋል። 24 በተፈጠረ ጊዜ መላእክቴ የሣቁበት፥ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ ምንም የለም። 25 ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፤ በውኃ ውስጥም ላሉ ሁሉ ንጉሥ ነው።” |