ኢዮብ 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔርም መለሰ፥ ኢዮብንም እንዲህ አለው፦ 2 “በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።” የኢዮብ መልስ 3 ኢዮብም መለሰ፥ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ 4 “አንተ ስታስተምረኝ እኔ የምመልሰው ምን አለኝ? ይህንስ እየሰማሁ ከእግዚአብሔር ጋር እከራከር ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? እጄን በአፌ ላይ ከማኖር በቀር የምመልሰው ምንድን ነው? 5 አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ ሁለተኛ ጊዜም ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።” እግዚአብሔር ለኢዮብ እንደ መለሰለት 6 እግዚአብሔርም እንደገና በደመና ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት፥ እንዲህም አለ፦ 7 “እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም መልስልኝ። 8 ወይም ፍርዴን መቃወምህን ተው፥ ጽድቅህ እንድትገለጥ እንጂ እኔ በሌላ መንገድ የምፈርድብህ ይመስልሃልን? 9 እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን? 10 እስኪ ልዕልናንና ኀይልን ተላበስ፤ በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ። 11 የቍጣህን መላእክት ላክ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ አዋርደው። 12 ትዕቢተኛውን ሰው ዝቅ ዝቅ አድርገው፤ ዝንጉዎችንም በአንድ ጊዜ አጥፋቸው። 13 በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤ ፊታቸውንም በኀፍረት ሙላ። 14 በዚያን ጊዜ ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል፥ እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ። 15 “እነሆ፥ በአንተ ዘንድ የዱር አውሬ አለ፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል። 16 እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኀይሉም በሆዱ እንብርት ውስጥ ነው። 17 ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹም ጅማት የተጐነጐነ ነው። 18 የጐድን አጥንቱ እንደ ናስ ነው፤ የጀርባው አጥንቶችም እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው። 19 ይህ የእግዚአብሔር የፍጥረቱ አውራ ነው። ከተፈጠረም በኋላ መላእክት ሣቁበት። 20 ወደ ረዥም ተራራ በወጣ ጊዜም በሜዳው ላሉ እንስሳት በጥልቁ ስፍራ ደስታን ያደርጋል። 21 ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገል፥ በቄጠማና በሸንበቆ ሥር ይተኛል። 22 ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎችም ይከብቡታል። 23 እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል። 24 ዐይኑ እያየ በገመድ ይያዛልን? አፍንጫውስ ይበሳልን? 25 “በውኑ ዘንዶውን በመቃጥን ታወጣለህን? በአፍንጫውስ ገመድ ታስራለህን? 26 ወይስ ስናጋ በጕንጩ ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር ከንፈሩን ትበሳለህን? 27 በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን? በጣፈጠ ቃልስ ይናገርሃልን? 28 በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘለዓለም ባሪያ ይሆን ዘንድ ትወስደዋለህን? 29 ከዎፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ እንደ ልጆች መጫወቻ ዎፍ ታስረዋለህን? 30 አሕዛብ ይመገቡታልን? ወይስ የፊንቄ ሰዎች ይካፈሉታልን? 31 ጀልባዎች ሁሉ ቢሰበሰቡ የጅራቱን ቍርበት ሊሸከሙት አይችሉም። አጥማጆችም ራሱን በመረብ መያዝ አይችሉም። 32 እጅህን በላዩ ጫን፤ በአፉ የሚያደርገውን ጦርነት አስብ፥ እንግዲህም ወዲህ አትድገም፥ አላየህምን? ስለ እርሱስ የተባለውን አላደነቅህምን? |