ኢዮብ 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤልዩስ የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፈራጅ መሆን እንደ ተናገረ 1 ኤልዩስ ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፤ እናንተም ዐዋቂዎች፥ መልካም ነገርን አድምጡ። 3 ጆሮ ቃልን ትለያለችና፥ ጕሮሮም የመብልን ጣዕም ይለያል። 4 ፍርድን ለራሳችን እንምረጥ፤ በመካከላችንም ምን እንደሚሻል እንወቅ። 5 ኢዮብ እንዲህ ብሎአልና፦ እኔ ጻድቅ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን ፍርዴን አስወገደ፤ 6 ፍርዴን ሐሰተኛ አደረገብኝ፤ በደልም ሳይኖርብኝ በግፍዕ መከራን እቀበላለሁ። 7 መሣለቅን እንደ ውኃ የሚጠጣት፥ እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው? 8 ፈጽሞ ያልበደለ፥ ግፍን ከሚሠሩም ጋር ያልተባበረ፥ ከኃጥኣንም ጋር ያልሄደ፥ ማን ነው? 9 ሰው ከእግዚአብሔር ጕብኝት ሲኖረው እግዚአብሔር አይጐበኘውም አትበል። 10 “ሰለዚህ እናንተ አእምሮ ያላቸሁ ሰዎች ስሙኝ፤ በእግዚአብሔርም ዘንድ ትበድሉ ዘንድ አትውደዱ። ሁሉን በሚችል አምላክ ፊትም ጻድቁን አታውኩት። 11 ለሰው ሁሉ እንደ ሥራው ይመልስለታል፥ ሰውንም እንደ መንገዱ ያገኘዋል። 12 በእውነት እግዚአብሔርን ግፍ እንደሚሠራ ታደርገዋለህን? ወይስ ምድርን የፈጠረ ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድን ያጣምማልን? 13 ከሰማይ በታች ያለውን ዓለም፥ በውስጡም ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? 14 በእርሱ ያለ መንፈሱን፥ ሊያጸናና ሊይዝ ቢወድድ፥ 15 ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይሞታል፥ ሟችም ሁሉ ወደ ተፈጠረበት መሬት ይመለሳል። 16 ያለዚያ ግን ተመከር፥ ይህንም ስማ፤ የንግግሬንም ቃል አድምጥ። 17 ግፍን የሚጠላ፥ ክፉዎችንም የሚያጠፋ፥ ለዘለዓለም ጻድቅ ነው። 18 ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ የሚለው፥ መኳንንቱንም፦ ክፉዎች ናችሁ የሚላቸው ኀጢአተኛ ነው 19 እርሱ ግን የክቡርን ሰው ፊት አያፍርም። ለታላቁም ክብር መስጠትን አያውቅም፥ ከፊታቸውም አይሸሽም። 20 የሚጮኸውንና ሰውን የማይሰማውን ከንቱ ነገር ያገኘዋል፥ በድሆች ላይ ክፉ አድርጎአልና። 21 እርሱ የሰዎችን ሥራ ይመረምራል፥ ከሚሠሩትም ሁሉ ከእርሱ የሚሰወር ምንም የለም። 22 ኀጢአትን የሚሠሩ የሚሰወሩበት ቦታ የለም። 23 ሁሉን ከሚያይ ከእግዚአብሔር አያመልጡምና። 24 እግዚአብሔር ወደ ታች ወደ ሰዎች ይመለከታል፥ ሊመረመሩ የማይችሉ ነገሮችን ሁሉ፥ ቍጥር የሌላቸውን የተከበሩትንና ድንቆችንም ያስተውላል። 25 ሥራቸውን ያውቃል፥ በእነርሱም ላይ ሌሊትን ያመጣል፥ መከራንም ያጸናባቸዋል። 26 ኃጥኣንን ያጠፋቸዋል፥ ጻድቃን ግን በፊቱ ናቸው። 27 ከእግዚአብሔር ሕግ ፈቀቅ ያሉ፥ ፍርዱን አያውቁም። 28 እርሱም የድሆችን ጩኸት በእነርሱ ላይ ይመልሳል፥ የችግረኞችንም ልቅሶ ይሰማል። 29 “እርሱ ዕረፍትን ይሰጣል፤ የሚፈርድስ ማን ነው? በሕዝብ ወይም በሰው ዘንድ ፊቱን ቢሰውር የሚያየው ማን ነው? 30 ስለ ሕዝቡም ክፋት፥ ግብዝ ሰውን ያነግሣል። 31 “ኀያሉ እግዚአብሔርን፦ እንዲህ የሚል አለ፥ እኔ በረከትን ተቀበልሁ፥ መያዣውንም አልወስድም። 32 እኔ ራሴ አያለሁ፥ ኀጢአትንም ሠርቼ እንደ ሆነ፥ ሐሰትንም ተናግሬ እንደ ሆነ፥ ደግሜ እንዳልሠራ አንተ አሳየኝ። 33 በውኑ አንተ ከእኔ ትርቅ ዘንድ፥ እኔ ከአንተ የተቀበልሁት አለን? አንተ ትመርጣለህ እንጂ እኔ አይደለሁምና፤ ስለዚህ የምታውቀው ካለ ተናገር። 34 የልብ ጥበበኞች እንዲህ ይላሉና፦ ጠቢብ ሰው ነገሬን ይሰማኛል። 35 ኢዮብ እንደ ጠቢብ በዕውቀት አይናገርም፥ ቃሉም እንደ ምሁር አይደለም። 36 ነገር ግን ኢዮብ ሆይ፥ ተማር። እንደ ሰነፎችም አትመልስ፥ 37 በኀጢአቶችህ ላይ እንዳትጨምር፥ በእግዚአብሔርም ፊት ብዙ መናገር በደል ይሆንብሃል።” |