ኢዮብ 30 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ምዕራፍ 30። 1 “አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ ለመዘባበት በእኔ ላይ ሳቁ፤ አባቶቻቸውን የናቅሁባቸውና እንደ መንጋዬ ውሾች ያልቈጠርኋቸው ዛሬ ለብቻቸው ይገሥጹኛል። 2 የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምንድን ነው? ሞት በላያቸው ይምጣ። 3 ትላንት በድካምና በውርደት ከምድረ በዳ ያመለጡ፥ ከረኃብ የተነሣ ተሰድደው ይለምናሉ። 4 እየዞሩ የሚለምኑና የሚበሉ በቅልውጥም የሚኖሩ ወራዶች፥ ዐመፀኞችና ከበጎ ነገሮች ሁሉ የተቸገሩ ናቸው። ከታላቅ ረኃብም የተነሣ ጨው ጨው የሚለውን የእንጨት ሥር ይበላሉ። 5 “ሌቦች በእኔ ላይ ተነሡ፥ 6 በሸለቆው ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ ውስጥ በዓለትም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ፤ 7 በገደል ማሚቶው መካከል ይጮኻሉ፤ በሳማ ውስጥም ይሸሸጋሉ። 8 የሰነፎችና የክፉዎች ሰዎች ልጆች ናቸው፤ ስማቸውና ክብራቸው ከምድር የጠፋ ነው። 9 አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው። 10 ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤ ምራቃቸውንም በፊቴ መትፋትን አልታከቱም። 11 የቀስቱን አፎት ከፍቶ ክፉ አደረገብኝ፤ በፊቴም ልጓሙን ሰደደ። 12 በኀይሉ ቀኝ ተነሣብኝ፤ እግሮቹንም ዘረጋብኝ፤ የሞትንም መንገድ በእኔ ላይ አደረገ። 13 ፍለጋዬን አጠፋ፤ ልብሴን ገፈፈኝ፥ በቀስቱም ነደፈኝ። 14 እንደ ወደደ አደረገብኝ፤ በመከራም እዛብራለሁ። 15 ድንጋጤ በላዬ ተመላለሰችብኝ፥ ነፍሴ ከእኔ ላይ እለይ እለይ አለች፥ ደኅንነቴም እንደ ተበተነ ደመና አለፈች። 16 “አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤ ጭንቀትም በእኔ ላይ ሞላ፤ 17 በሌሊት ሁሉ አጥንቶች በደዌ ይነድዳሉ፥ ጅማቶችም ይቀልጣሉ። 18 ከታላቁ ደዌ ኀይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤ የልብሴ ክሳድ አነቀችኝ፥ ቀሚሴም በአንገቴ ተጣበቀ። 19 እርሱ እንደ ጭቃ ረገጠኝ፥ ዕድል ፋንታዬም አፈርና አመድ ሆነ። 20 ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልሰማኸኝምም፤ እነርሱ ግን ቆመው ተመለከቱኝ። 21 ምሕረት የሌላቸው ሰዎች ደበደቡኝ፥ የገረፈችኝ እጅም በረታች። 22 በኀዘን አኖርኸኝ፥ ከሕይወቴም አራቅኸኝ። 23 ሞት እንደሚያጠፋኝ አውቃለሁና ለሟችም ሁሉ ማደሪያው ምድር ናትና። 24 እኔ ራሴ ልታነቅ በወደድሁ ነበር ይህም ባይሆን ሌላው እንዲሁ እንዲያደርግልኝ እለምናለሁ። 25 ረዳት ለሌለው ሰው አለቀስሁ የተቸገረ ሰውን ባየሁ ጊዜ ጮኽሁ። 26 ነገር ግን በጎ ነገርን በተጠባበቅኋት ጊዜ እነሆ ክፉ ቀኖች መጡብኝ፤ ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ፥ ጨለማም መጣብኝ። 27 ሆዴ ፈላች፥ አላረፈችምም፤ የችግርም ዘመን መጣችብኝ። 28 በጠባቡ ሄድሁ፥ የሚያሰፋልኝም አጣሁ፥ በጉባኤም መካከል ቆሜ እጮኻለሁ። 29 ለሌሊት ዎፍ ወንድም፥ ለሰጎንም ባልንጀራ ሆንሁ። 30 ቍርበቴ እጅግ ጠቈረ፥ አጥንቶቼም ከትኩሳት የተነሣ ተቃጠሉ። 31 ስለዚህ ሕማሜ መሰንቆ፥ ልቅሶዬም በገና ሆነብኝ። |