ኢዮብ 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮብ መልስ 1 ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “ማንን ትደግፋለህ? ማንንስ ልትረዳ ትወድዳለህ? ጥንቱን ኀይሉ ብዙ፥ ክንዱም ጽኑ የሆነ እርሱ አይደለምን? 3 ለማንስ ታማክራለህ? ጥበብ ሁሉ ለእርሱ አይደለምን? ማንንስ ትከተላለህ? ታላቅ ኀይል ያለው እርሱ አይደለምን? 4 ነገርን ለማን ትናገራለህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ይወጣል? 5 ኀያላን ከውኆች በታች፥ በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ ይወለዳሉን? 6 ሲኦል በፊቱ ራቁቱን ነው፥ ሞትንም ከእርሱ የሚጋርደው የለም። 7 ሰማይን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም አንዳች አልባ ያንጠለጥላል። 8 ውኃውን በደመና ውስጥ ይቋጥራል፥ ደመናውም ከታች አይቀደድም። 9 የዙፋኑን ፊት ይከድናል፥ ደመናውንም ይዘረጋበታል። 10 ብርሃን ከጨለማ እስከሚለይበት ዳርቻ ድረስ፥ የውኃውን ፊት በተወሰነ ትእዛዙ ከበበው። 11 የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ። 12 በኀይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥ በማስተዋሉም ዐንበሪውን ይገለብጠዋል። 13 የሲኦል በረኞች ለእርሱ አደሉ። በትእዛዙም ዐመፀኛውን እባብ ገደለው። 14 እነሆ ይህ የመንገዱ ክፍል ነው፤ የቀሩትንም ነገሮቹን እንሰማለን፤ በሚያደርግበትስ ጊዜ የነጐድጓዱን ኀይል የሚያውቅ ማን ነው?” |