ኢዮብ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “ዛሬም ዘለፋዬ ከእጄ እንደ ሆነ ዐወቅሁ። እጁንም በእኔ ላይ አከበደ፥ አስለቀሰኝም። 3 እርሱን ወዴት እንደማገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ነገሩ ፍጻሜም ምነው በደረስሁ! 4 የሠራሁት ቢኖር ይነግረኝ ነበረ፥ ስከራከርም አፌ ዝም አይልም ነበር። 5 የሚሰጠኝንም ፈውስ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር። 6 በኀይሉ ብዛት ቢመጣብኝም እንኳ በቍጣው አያስፈራራኝም ነበር። 7 እውነትና ቅንነት ከእርሱ ዘንድ ናቸውና። ከፍርዴም ለዘለዓለም ያሳርፈኝ ነበር። 8 እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እንግዲህም አልኖርም፤ ስለ ፍጻሜውም አላውቅም፤ 9 ወደሚሠራበትም ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤ ቀኝ እጁ ይከብበኛል፤ ነገር ግን አላየውም። 10 መንገዴን ፈጽሞ ዐወቀ፥ እንደ ወርቅም ፈተነኝ 11 እንደ ትእዛዙ እወጣለሁ፥ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም። 12 ከትእዛዙም አላለፍሁም፤ ቃሉን በልቤ ሰውሬአለሁ። 13 “ስለ ፍርድ የሚከራከር ማን ነው? እርሱ የወደደውን ያደርጋልና። 14 ስለዚህም እኔ ስለ እርሱ ቸኰልሁ፤ በተገሠጽሁም ጊዜ አሰብሁት። 15 ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤ አስበዋለሁ፤ ከእርሱም የተነሣ እፈራለሁ። 16 እግዚአብሔር ግን ልቤን አቀለጠው፥ ሁሉን የሚችል አምላክም አስጨንቆኛል። 17 ጨለማም እንደሚመጣብኝ፥ ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን እንደሚከድን አላወቅሁም። |