ኢዮብ 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሦስተኛው ዙር ንግግር 1 ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “በውኑ ማስተዋልንና ዕውቀትን የሚያስተምር፥ እግዚአብሔር አይደለምን? 3 አንተ በሥራህ ንጹሕ ከሆንህ እግዚአብሔርን ምን ያገደዋል? መንገድህንስ ብታቀና ምን ይጠቅመዋል? 4 አንተንስ ተቈጣጥሮ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን? 5 “ክፋትህስ የበዛ አይደለምን? ኀጢአትህስ ቍጥር የሌለው አይደለምን? 6 የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥ የታረዘውንም ልብሱን ገፍፈሃል። 7 ለተጠማ ውኃ አላጠጣህም፥ የራብተኛውንም ጕርሻ ነጥቀሃል፥ ምድርን የሚዘራ ሰውም በውስጧ ድንበርን ያኖራል። 8 ፊታቸውን አይተህ ያደነቅሃቸው አሉ፥ በምድርም ላይ ድሆችን በዐመፅ ጠላህ 9 መበለቶችን ባዶአቸውን ሰድደሃቸዋል፥ ድሃአደጎችንም አስጨንቀሃቸዋል። 10 ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ ከባድ ጦርነትም አናውጦሃል። 11 ብርሃኑም ጨለማ ሆነብህ፥ ተኝተህም ሳለህ ውኃው አሰጠመህ። 12 “ልዑል የወደደውን ያደርግ ዘንድ የሚገባው አይደለምን? ትዕቢተኞችንስ አያዋርዳቸውምን? 13 አንተም እንዲህ ብለሃል፦ ኀያል እርሱ ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን? 14 የጠቈረ ደመና ጋርዶታል አያይምም፤ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል። 15 በውኑ ጻድቃን ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን? 16 ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ። 17 እግዚአብሔር ምን ያደርገናል? ሁሉን የሚችል አምላክስ ምን ያመጣብናል? ይላሉ። 18 ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤ የኃጥኣን ምክር ከእርሱ የራቀች ናት። 19 ጻድቃንም አይተው ሳቁ፤ ንጹሓንም በንቀት ይዘባበቱባቸዋል። 20 በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥ የቀረውንም እሳት በላች። 21 “አሁንም መታገሥ ትችል እንደ ሆነ፥ ፍሬህም ይበጅ እንደ ሆነ እስኪ ጽኑ ሁን። 22 ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ 23 ብትመለስ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ብታዋርድ፥ ኀጢአትንም ከልብህ ብታርቅ፥ 24 በዓለቱ ቋጥኝ ላይ ለራስህ መዝገብን ታኖራለህ። የሶፎርም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ይሆንልሃል። 25 ሁሉን የሚችል አምላክም ከጠላቶችህ ይረዳሃል። ንጽሕናንም በእሳት እንደ ተፈተነ ብር አድርጎ ይመልስልሃል። 26 በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ታገኛለህ። ወደ ሰማይም በደስታ ትመለከታለህ። 27 ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ይሰጠሃል። 28 የጽድቅህንም ብድራት ይሰጥሃል። ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል። 29 ራስህን ብታዋርድ ሰውም ኰራብኝ ብትል፥ ራሱን የሚያዋርደውን ሰው ያድነዋል። 30 ንጹሕን ሰው ያድነዋል፤ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።” |