ኢዮብ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ከሴት የተወለደ ሟች ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ነው፥ የቍጣ መከራንም የተሞላ ነው። 2 እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ያልፋል፥ እርሱም አይኖርም። 3 እንደዚህስ ያለውን ሰው አንተ የምትመረምረው አይደለምን? በፊትህስ እርሱን ወደ ፍርድ ታገባዋለህን? 4 ከርኵሰት የሚነጻ ማን ነው? አንድ ስንኳ የለም። 5 በምድር ላይ አንድ ቀንም እንኳ ቢኖር፤ ወሮቹም በአንተ ዘንድ የተቈጠሩ ናቸው፤ ዘመኑንም ወስነህ ትሰጠዋለህ፤ እርሱም ከዚያ አያልፍም። 6 “እንደ ምንደኛ ሕይወቱን እንዲጠባበቃት፥ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ዘወር በል። 7 ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ተስፋ አለው፤ ቅርንጫፉም አያልቅም። 8 ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በጭንጫ ውስጥ ቢሞት፥ 9 ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አዲስ ተክልም ያፈራል። 10 ሰው ግን ከሞተ ፈጽሞ ይተላል፤ ሟች ሰው ከሞተ በኋላ እንግዲህ አይኖርም። 11 ባሕር ይጐድላል፤ ወንዙም ይነጥፋል፤ ይደርቅማል። 12 ሰውም ከተኛ በኋላ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም። 13 “በመቃብር ውስጥ ምነው በጠበቅኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪበርድም ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! እስከምታስበኝም ምነው ቀጠሮ በሰጠኸኝ ኖሮ! 14 ሰው የሕይወቱን ዘመን ፈጽሞ ከሞተ በኋላ በሕይወት የሚኖር ቢሆን ዳግመኛ እስክወለድ ድረስ፥ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። 15 በጠራኸኝም ጊዜ በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ አትናቀኝ። 16 አሁን ግን ኀጢአቶችን ቈጥረሃል፤ ከበደሌም እንዲቱንስ እንኳ አልረሳህም። 17 መተላለፌን በከረጢት ውስጥ አትመሃል፥ ኀጢአቴንም ለብጠህባታል። 18 ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፤ 19 “ውኆች ድንጋዮችን ይፍቃሉ፤ ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤ እንዲሁ አንተ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ። 20 ለዘለዓለም ታስወግደዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ ፊትህን ትመልስበታለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ። 21 ልጆቹ ቢበዙ አያያቸውም ቢያንሱም አያውቃቸውም። 22 ነገር ግን የገዛ ሥጋው በሕማም ይሠቃያል፥ ነፍሱም ታለቅሳለች።” |