ኢዮብ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ነፍሴ ስለ ተጨነቀች ቃሌን በእንጕርጕሮ አሰማለሁ፤ ነፍሴም እየተጨነቀች በምሬት እናገራለሁ። 2 እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦ ኀጢኣተኛ እንድሆን አታስተምረኝ፤ ለምንስ እንደዚህ ፈረድህብኝ? 3 ኀጢኣተኛ ብሆን በአንተ ዘንድ መልካም ነውን? የእጅህን ሥራ ቸል ብለሃልና፤ የኃጥኣንንም ምክር ተመልክተሃልና። 4 በውኑ የሰው ዐይን አለህን? ወይስ መዋቲ ሰው እንደሚያይ ታያለህን? 5 ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን? 6 ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥ ኀጢኣቴንም ትመረምር ዘንድ፥ 7 ከዚህ በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ አንተ ታውቃለህ። ነግር ግን ከእጅህ የሚያመልጥ ማን ነው? 8 “እጆችህ ፈጠሩኝ፤ ሠሩኝም፤ ከዚያም በኋላ ዞረህ ጣልኸኝ። 9 ከጭቃ እንደ ፈጠርኸኝ አስብ፤ ዳግመኛም ወደ ትቢያ ትመልሰኛለህ፤ 10 በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን? 11 ቍርበትና ሥጋን አለበስኸኝ፤ በአጥንትና በዥማትም አጠነከርኸኝ። 12 ሕይወትና ቸርነትን ሰጠኸኝ። መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀልኝ። 13 ይህ ሁሉ በአንተ ዘንድ አለ። ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፥ የሚሳንህም እንደ ሌለ አውቃለሁ። 14 ኀጢኣት ብሠራ አንተ ትጠባበቀኛለህ፤ ከኀጢኣቴም ንጹሕ አታደርገኝም። 15 በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፤ ጕስቍልናንም ጠገብኋት። 16 ለመገደል እንደ አንበሳ ታደንሁ። ተመልሰህም ፈጽመህ ታጠፋኛለህ። 17 ዳግመኛም ከጥንት ጀምሮ ትመረምረኛለህ፤ ታላቅ መቅሠፍትን አመጣህብኝ። ፈተናዎችንም ላክህብኝ። 18 “ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዐይንም ሳያየኝ ለምን አልሞትሁም? 19 እንዳልነበረስ ለምን አልሆንሁም? ከማኅፀንም ወደ መቃብር ለምን አልወረድሁም? 20 የሕይወቴ ዘመን አጭር አይደለምን? ጥቂት አርፍ ዘንድ ተወኝ፤ 21 ወደማልመለስበት ስፍራ፥ ወደ ጨለማና ወደ ጭጋግ ምድር፥ 22 የዘለዓለም ጨለማም ወደ አለባት፥ ብርሃንም ወደሌለባት፥ ማንም የሟችን ሕይወት ወደማያይባት ምድር ሳልሄድ ጥቂት አርፍ ዘንድ ተወኝ።” |