ኢዮብ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢዮብ እንደ ተፈተነ 1 አውስጢድ በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። 2 ሰባትም ወንዶች፥ ሦስትም ሴቶች ልጆች ነበሩት። 3 ከብቶቹም፦ ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበሩ፤ እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት፤ ሥራውም በምድር ላይ ታላቅ ነበረ፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገናና ነበረ። 4 ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በእያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውንም ከእነርሱ ጋር ይወስዱአቸው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር ይበሉና ይጠጡ ነበር። 5 የግብዣውም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ኢዮብ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ በማለዳም ገሥግሦ፦ ስለ ልጆቹ በቍጥራቸው መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ አንድ ወይፈን ስለ ነፍሳቸው የኀጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ኢዮብ፥ “ምናልባት ልጆቼ በልባቸው በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር ያስቡ ይሆናል” ይል ነበርና። 6 ከዕለታት አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፤ ሰይጣንም ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጣ። 7 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፥ “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ ከሰማይ በታችም ተመላለስሁና መጣሁ።” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 8 እግዚአብሔርም ሰይጣንን አለው፥ “በባሪያዬ በኢዮብ ላይ የምታስበው ነገር እንዳይኖር ተጠንቀቅ! በምድር ላይ እንደ እርሱ ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ሰው የለምና።” 9 ሰይጣንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብሎ መለሰ፥ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመልከው በከንቱ ነውን? 10 አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም፥ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። 11 ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” 12 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “እነሆ፥ ለእርሱ ያለውን ሁሉ በእጅህ ሰጠሁህ፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ። የኢዮብ ንብረት እንደ ጠፋና ልጆቹ እንደ ሞቱ 13 አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። 14 መልእክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ፥ “ጥምድ በሬዎችህ እርሻ ያርሱ ነበር፥ በአጠገባቸውም ሴቶች አህዮችህ ይሰማሩ ነበር፤ 15 ማራኪዎችም መጥተው ወሰዱአቸው፥ ብላቴኖችህንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ” አለው። 16 እርሱም ገና ይህን ሲናገር ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፦ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎችህንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችህንም በላች፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።” 17 እርሱም ገና ይህን ሲናገር ሦስተኛው መልእክተኛ መጥቶ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “ፈረሰኞች በሦስት ረድፍ ከብበው ግመሎችን ማርከው ወሰዱ፥ ብላቴኖችህንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።” 18 እርሱም ገና ይህን ሲናገር አራተኛው መልእክተኛ መጥቶ ለኢዮብ እንዲህ አለው፥ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ሲበሉና የወይን ጠጅ ሲጠጡ፥ 19 እነሆ፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ ድንገት መጥቶ ቤቱን በአራት ማዕዘኑ መታው፥ ቤቱም በብላቴኖቹ ላይ ወደቀ፥ እነርሱም ሞቱ፤ እኔም ብቻዬን አምልጬ እነግርህ ዘንድ መጣሁ።” 20 ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 21 እንዲህም አለ፥ “ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ የእግዚአብብሔር ስም የተባረከ ይሁን።” 22 በዚህም በደረሰበት ሁሉ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም። |