ኢሳይያስ 65 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ዐመፀኞችን እንደሚቀጣ 1 ያልፈለጉኝ አገኙኝ፤ ላልጠየቁኝም ተገኘሁ፤ ስሜን ላልጠራ ሕዝብ፥ “እነሆኝ” አልሁት። 2 በጽድቅ መንገድ ወደማይሄዱ፥ ኀጢአታቸውን ወደሚከተሉ ዐመፀኞች ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆችን ዘረጋሁ። 3 እኒህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ ለአጋንንት የሚያጥኑ፥ 4 በመቃብርም መካከል የሚተኙ፥ በዋሻ ውስጥ የሚያልሙ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የመሥዋዕታቸውን ደምና ዕቃቸውንም ሁሉ ያረክሳሉ። 5 “እኔ ንጹሕ ነኝና ከእኔ ራቁ፥ ወደ እኔም አትቅረቡ” ይላሉ። ስለዚህም የቍጣዬ ጢስ በዘመኑ ሁሉ እንደ እሳት ይነድድባቸዋል። 6 እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል፦ ኀጢአቶቻችሁንና የአባቶቻችሁን ኀጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ እመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ 7 በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ አሽሟጠጡኝ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ። 8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የወይን ፍሬ በዘለላው በተገኘች ጊዜ፦ በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ ባሪያዎች እንዲህ አደርጋለሁ። 9 የያዕቆብን ዘርና የይሁዳን ዘር አመጣለሁ፤ የተቀደሰው ተራራዬንም ይወርሳሉ፤ እኔ የመረጥኋቸውና ባሪያዎችም ይወርሱአታል፤ በዚያም ይኖራሉ። 10 በመንጋው መሰማሪያና በዛፍ መካከል በአኮር ሸለቆና በቆላውም የላሞች መመሰግያ ለፈለጉኝ ሕዝቤ ይሆናል። 11 “እናንተ ግን እኔን ተዋችሁኝ፤ ቅዱሱንም ተራራዬን ረሳችሁ፥ ለአጋንንትም ማዕድ አዘጋጃችሁ፤ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ቀዳችሁ፤ 12 እኔም ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ሁላችሁም በሰይፍ ትገደላላችሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገር አደረጋችሁ፤ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።” 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ ባሪያዎች ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎች ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎች ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ትጐሰቍላላችሁ፤ 14 እነሆ፥ ባሪያዎች ሐሤት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ! ትላላችሁ። 15 ስማችሁንም እኔ ለመረጥኋቸው ሕዝቤ ጥጋብ አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ያጠፋችኋል፤ ባሪያዎች ግን በሐዲስ ስም ይጠራሉ። 16 እንዲሁም በምድር ላይ የተባረኩ ይሆናሉ፤ እውነተኛውን አምላክ ያመሰግናሉና፥ በምድርም ላይ በእውነተኛው አምላክ ይምላሉና፤ የቀድሞውንም ጭንቀት ረስተዋልና፤ በልቡናቸውም አያስቡትምና። 17 “እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይሆናልና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም። 18 ነገር ግን በውስጥዋ ደስታንና ሐሤትን ያገኛሉ፤ እኔም ለኢየሩሳሌም ደስታን ለሕዝቤም ሐሤትን አደርጋለሁ። 19 እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም። 20 ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጐልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኀጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። 21 ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። 22 ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፤ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ሕይወት ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረዥም ዘመን ደስ ይላቸዋል። 23 እነርሱ ከእነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም፤ ለርግማንም አይወልዱም። 24 “እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፤ ገናም ሲናገሩ እነሆ፥ አለሁ እላቸዋለሁ። 25 ያንጊዜ ተኵላና በግ በአንድነት ይሰማራሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፤ አያጠፉምም፥” ይላል እግዚአብሔር። |