ኢሳይያስ 64 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ሰማይን ብትከፍት ከአንተ የተነሣ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ ይቀልጣሉም። 2 አደሮ ማር በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ እንዲሁ ጠላቶችህን እሳት ትበላቸዋለች፤ ስምህም በእነርሱ ላይ ይታወቃል፤ አሕዛብም በፊትህ ይደነግጣሉ። 3 የክብርህንም ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ተራሮች በፊትህ ተንቀጠቀጡ። 4 ከጥንት ጀምሮ ይቅርታህን ለሚጠባበቁ ምሕረትን ከምታደርግላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ አላየንም፤ አልሰማንምም። 5 በቸርነትህ የሚታገሡ መንገድህንም የሚያስቡ ይገናኙሃል፤ እነሆ፥ አንተ ተቈጣህ፤ እኛም ኀጢአት ሠራን፤ ስለዚህም ተሳሳትን። 6 ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ በኀጢአታችን ምክንያት እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ እንዲሁም ነፋስ ጠራርጎ ወስዶናል። 7 ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ መልሰሃል፤ ለኀጢአታችንም አሳልፈህ ሰጥተኸናል። 8 አሁን ግን፥ ጌታ ሆይ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። 9 አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፤ ለዘለዓለምም ኀጢአታችንን አታስብ፤ አሁንም እባክህ፥ ወደ እኛ ተመልከት፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። 10 የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። 11 አባቶቻችን ያከበሩት ክብራችን ቤተ መቅደስህ በእሳት ተቃጥሎአል፤ ያማረውም ስፍራችን ፈርሶአል። 12 አቤቱ፥ በዚህ ነገር ሁሉ ታገሥኸን፤ ዝም አልኸን፤ እጅግም አዋረድኸን። |